ኢንስቲትዩቱ ለጤና ተቋማት ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

145

ባህር ዳር ግንቦት 4/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ለወደሙ የጤና ተቋማት 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የላቦራቶሪ መሳሪያዎችና ማሽኖች ድጋፍ አደረገ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ርክክብ ሥነሥርዓት ላይ እንዳሉት በክልሉ በጦርነቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት የጤናው ዘርፍ አንዱ ነው።

በጦርነቱ በርካታ የጤና ተቋማት የህክምና መገልገያ ቁሳቁስና መሰረተ-ልማት ለውድመትና ዘረፋ በመዳረጋቸው መልሶ ለማቋቋም እየተዳረገ ያለው ጥረት የሁሉንም ድጋፍና ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።

መንግሥት በጦርነቱ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት ዘርፈ ብዙ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንስቲትዩቱ ያደረገው ድጋፍም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በላቦራቶሪ ዘርፍ በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

ጦርነቱ  በጤናው ዘርፍ ጉዳት ካደረሰባቸው የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የላቦራቶሪ አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቱን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ህይወት ደበበ ናቸው።

ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ድንገተኛ የህክምና አገልግሎት መልሶ አደራጅቶ ሥራ ለማስጀመር ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በባለድርሻ አካላት ርብርብ መደረጉን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ አሁንም ድጋፉ እንዲቀጥል ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ጠይቀዋል።

በኢንስቲትዩቱ የተደረገው ድጋፍ የህክምና ተቋማትን ላቦራቶሪ መልሶ ለማደራጀት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ የጎላ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ናቸው።

ኢንስቲትዩቱ የለገሳቸው መሳሪያዎች በፍጥነት ለታለመላቸው ዓላማ እንደሚውሉ አረጋግጠው፤ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።