በአፋር ክልል በሽባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት የሕፃናት ክትባት ተደራሽነት ቀንሷል

147

ሰመራ፤ ግንቦት 4/ 2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል በሽባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት የሕጻናት ክትባት ተደራሽነት መቀነሱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው  የአፍሪካ ክትባት ሳምንት በክልል ደረጃ በሰመራ ከተማ ዛሬ ተከብል።
የቢሮ ኃላፊው አቶ ያሲን ሀቢብ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በክልሉ የፈጸመው ወረራ የጤናውን ጨምሮ ሁሉንም  ዘርፎች  ጎድቷል።

በክልሉ ሕዝብ ሲገለገልባቸው የነበሩ ምጣኔ ኃብታዊና ማህበራዊ ተቋማት እንዲሁም የመሰረተ ልማት አውታሮችን በማፍረስ፣ በማውደምና በመዝረፍ  ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረስ ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረጉን ገልጸዋል።

ከሰባዊ ድጋፉ ሥራ ጎን ለጎን በሽብር ቡድኑ ከወደሙ የጤና ተቋማት ውስጥ አንድ ሆስፒታልና 17 ጤና ጣቢያዎችን መልሶ በማደራጀትና ማቋቋም ወደስራ አንዲገቡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ ባደረሰው መጠነሰፊ ውድመትና በደቀነው የደህንነት ስጋት ምክንያት የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ  አስተዋጽኦ ያላቸው የክትባት ስራዎችን ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን አስረድተዋል።
በመሆኑም መርሃ ግብሩን ተደራሽ የማድረጉ ሥራ የባለድርሻ አካላትን ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተዋል።

በየደረጃው የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የክትባት መርሃ ግብሮችን ተደራሽ እንዲሆኑ በኃላፊነትና በቁርጠኝነት መስራትና መምራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንበዋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶችና ሕፃናት ክትባት ዳይሬክተር አቶ አወል ጉደሌ በበኩላቸው በክልሉ በ2013 ዓ.ም የሁሉም አይነት መደበኛ የሕፃናት ክተባት 82 በመቶ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመት  የክትባቱን ተደራሽነት 100% ለማድረስ የታቀደ ቢሆንም እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ማሳካት የተቻለው የዕቅዱ 39 በመቶ ያህል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሓት በክልሉ በተለያዩ  ወረዳዎች በፈጸመው ተደጋጋሚ ወረራና ጥቃት፣ የተፈጸመው ዘረፋና ውድመት ለውጤቱ መቀነስ ተጠቃሽ ምክንያት ነው ብለዋል።
በክልሉ የመደበኛ ክትባት ሂደቱን ለማገዝ ክትባት ያቋረጡ ልጆችን የልየታ ስራ እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ  የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ደረጀ በለው ናቸው።

ዶክተር ደረጀ አክለውም በጦርነቱ ቀጣና ውስጥ ለነበሩ ጤና ባለሙያዎች የስልጠና ድጋፍም እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የፓዝ-ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ደሪባ አስረስ በበኩላቸው በጦርነት ውስጥ በነበሩት ጭፍራና እዋ ወረዳ ከሚመለከታቸው አካላት ጋረ  በመተባበር  ለሕፃናት ክትባቱን ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።
በክልሉ የተቀዛቀዘውን የሕፃናት መደበኛ ክትባት መርሃ ግበር ለማነቃቃት የህዝብ ንቅናቄ ስራዎች እንደሚሰሩም አስታውቀዋል።
በክልሉ ክትባት ያቋረጡ ጨቅላ ሕፃናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሕፃናት አድን ድርጅት ተወካይ ወይዘሮ ምዕራብ ሰለሞን ገልጸዋል።

የኃይማኖት አባቶችንና የባህላዊ መሪዎችን በመጠቀም የማህበረሰብ ንቅናቄ ስራዎችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እየደገፉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

መድረኩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አጋር አካላትን ቅንጂታዊ አሰራር ለማጎልበት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።

በክልሉ ያለውን ዝቅተኛ የሕፃናት ክትባት ሽፍን ማሻሻልን ዓላማ ባደረገው ሥነ-ሥርዓት ላይ የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧዋል።