በኢትዮጵያና ቻይና መካከል የተደረጉት የኢንቨስትመንት ስምምነቶች በሀገራቱ የኢኮኖሚ ትስስር ላይ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍቱ ናቸው

196

ግንቦት 04/2014(ኢዜአ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል የተደረጉት የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ለሀገራቱ ኢኮኖሚያዊ ትስስር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍቱ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ኢትዮጵያና ቻይና  በኢንቨስትመንት መስክ በጋራ ለመስራት የሚያስችሏቸውን ስድስት አዳዲስ ስምምነቶች ዛሬ ተፈራርመዋል ።

በኢንዱስትሪ፣ በፋርማሲቲካል፣ በማኑፋክቸሪንግ ፣ በግብርና፣ በመሰረተ ልማትና በጤና መስኮች ላይ የሚተገበሩ ስምምነቶች ሲሆኑ በቻይና ኩባንያዎች ተወካይና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ተፈርመዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረጓን ተከትሎ ለውጭ ኢንቨስትመንት ይበልጥ ሳቢ እየሆነች መምጣቷን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው የተደረገው ስምምነት በተለይ በኢኮኖሚው መስክ የተጀመረውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሺነር ሌሊሴ ነሜ፤ ቻይና ለኢትዮጵያ እውነተኛ የልማት አጋር ብቻ ሳትሆን የልማት ፖሊሲዎችን በመቅረጽና ድህነትን በመቀነስ ተምሳሌት ናት ብለዋል።

የተደረጉት ስምምነቶችም የሀገሪቷን የማምረት አቅም ለመጨመርና በተለያዩ መስኮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያግዝ ይሆናል ነው ያሉት።   

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን፤ በኢትዮጵያ የቻይናን ባለሀብቶች በስፋት ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማድረጋቸው አመስግነዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና በኢንዱስትሪ፣ በመሰረተ ልማት፣ በማኑፋክቸሪንግና ሌሎችም ዘርፎች በጋራና በትብብር ለመስራት የተስማሙባቸው ዋና ዋና መስኮች መሆናቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም