የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዜጎችን አብሮነት ማጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ተጠየቀ

97

ሆሳዕና ፤ ግንቦት 4/2014 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያዎች የዜጎችን አብሮነትና መልካም አስተዳደር ማጠናከር ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ተጠየቀ።

በሀድያ ዞን  ከሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ዘርፍ  የተወጣጡ ባለሙያዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ መድረኩ የሀድያ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ ሎንበሶ እንዳሉት ፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ  በህብረተሰቡ  ቅሬታ የሚነሳባቸው ተቋማትን በማጋለጥ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ማዋጣት ይጠበቅባቸዋል።

በተለይም የዜጎችን አብሮነት በሚያጠናክሩና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ በሚያስገኙ ዘገባዎች ላይ በማተኮር ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ካሳሁን አባይነህ በበኩላቸው፤ የጋዜጠኝነት መርህን የተከተለ መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስና ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ውስንነት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡን ከሀሰተኛ የመረጃ ምንጮች  መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን  ባለሙያዎች  በማህበራዊ የትስስር ገፆች የሚናፈሱ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመመከት ሙያዊ  ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተመልክቷል።

በደቡብ  ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት  የሆሳዕና ቅርንጫፍ ጋዜጠኛ አብርሃም ሙጎሮ፤ መገናኛ ብዙሃን ተጨባጭ መረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ  በማድረግ የዜጎችን አብሮነት በማጠናከር ሚናችንን  በተገቢው መወጣት ይጠብቅብናል ነው ያለው።

በአገልግሎት አሰጣጥና ያለተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህዝብን ለምሬት የሚዳርጉና ቅሬታ የሚፈጥሩ አካላትን በመለየት የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጥ መስራትም እንዲሁ።

በውይይት መድረኩ የደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሆሳዕና ቅርንጫፍ፣ የዞኑ ኮሙዩኒኬሽንና ሌሎችም የዘርፉ   ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም