ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ አበረታች ስራዎችን እያከናወነች ነው- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

137

ሐረር ፤ ግንቦት 4/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ አበረታች ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደሩ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የሳምንቱ   ዋና  ዋና ጉዳዮች ላይ ዛሬ  በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ መግለጫቸው የብሔራዊ ጥሰትን ለመከላከል እንዲያመች  የሚኒስትሮች ታክስ ፎርስ ተቋቁሞ እየተሰራ  እንደሚገኝ  ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በዲፕሎማሲው መስክ አበረታች ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን ገልጸው፤ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ በርካታ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በታንዛንያ በእስር ላይ የሚገኙ 4ሺህ 500 ኢትዮጵያኖችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በሚቻልበት  ሁኔታ ምክክር መደረጉንም ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ረገድ የተከናወኑ ዋና  ዋና ተግባራትን አብራርተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም መከበር  በጎ እርምጃዎችን  ቢወስድም በአሸባሪው ህወሃት በኩል ግን አፍራሽ ተግባር እየተከናወነ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስት ለዘላቂ ሰላም ባለው ቁርጠኝነት የብሔራዊ ድርድር ኮሚሽን መስርቶ ወደ ስራም መገባቱንም ጠቅሰዋል።

በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ያልተገደበ  ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

በድርቅና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ለችግር  ለተጋለጡ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን አምባሳደር ዲና  አመላክተዋል።

በዚህ ረገድ መንግስት በሀገር ውስጥ  ስንዴ በማምረት   እራስን ለመቻል የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ  አብራርተዋል።

በሳምንቱ በምጣኔ ሀብት ዲፕሎማሲ የተከናወኑ ተግባራትንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው  አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም