መጽሐፍትን በመለገስ ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም ሊረባረብ ይገባል

157

ግንቦት 04/2014 (ኢዜአ)  መጽሐፍትን በመለገስ ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ሲሉ ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት መጽሐፍትን የለገሱ ግለሰቦች ተናገሩ።

የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍትን ለማጠናከር ከግለሰቦች ጀምሮ የተለያዩ ተቋማት መጽሐፍቶችን እያበረከቱ ይገኛሉ።

ኢዜአ ለቤተ-መጽሐፍት ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ በርከት ያሉ መጽሐፍትን ያበረከቱ ግለሰቦችን አናግሯል።

መጽሐፍትን በመለገስ ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ቤዛ ታዬ ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት 950 መጽሐፍቶችን መለገሷን ትናገራለች።

ተማሪ ቤዛ እንደምትናገረው ለቤተ-መጽሐፍቱ ያበረከተቻቸው መጽሐፍቶች ቤተሰቦቿ የተጠቀሙባቸውና እሷም በአብዛኛው ያነበበቻቸው እንደሆኑ ተናግራለች።

የመጽሐፍቱ ይዘቶችም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለምርምር የሚረዱና የተለያዩ ልቦለድ መጽሐፍቶች እንደሆኑ ገልጻለች።

ይህን በማድረጓ ትልቅ እርካታ እንደተሰማት የተናገረችው ተማሪ ቤዛ ''መጽሐፍቶች ትውልድን የሚያንጹና  ትውልድን የሚገነቡ ሀብቶች ናቸው'' ብላለች።

በተጨማሪም የሚያነብ ትውልድ የሚወስነው ውሳኔ  ሚዛናዊ መሆኑን አክላለች።

መጽሐፍቶች አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድም የሚጠቅሙ በመሆናቸው ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብላለች።

ሰዎች ቤታቸው አንብበዋቸው ያስቀመጧቸው መጽሐፍቶችን ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርባለች። 

በተመሳሳይም ከ500 መጽሐፍቶች በላይ ለአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ካበረከቱት ድርጅቶች መካከል አንዱ 'ቡክ ኮርነር' መጽሐፍ መደብር  ነው።

የ'ቡክ ኮርነር' መጽሐፍ መደብር ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ኩምሳ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ የህጻናት መማሪያ መጽሐፍትን ለግሰዋል።

ሀገርን ለማሳደግ፣ የሰለጠነ፣ እውቀት ያለው፣ ብቁ ትውልድ ለመፍጠር መጽሐፍት ትልቅ ጥቅም እንዳላቸው ይገልጻሉ።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ቤተ-መጽሐፍት ሰዎች ጊዜያቸውን በንባብና በመመራመር እንዲያሳልፉ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው።

በተለይ እንደዚህ አይነት ቤተ-መጽሐፍት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎችና በመዲናዋም በርከት ቢሉ መልካም መሆኑን ጠቅሰዋል።       

በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው አብርሆት ሁለገብ ቤተ-መጽሐፍት ታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።

ቤተ-መጽሐፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጽሐፍትን መያዝ የሚችል ሲሆን 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መደርደሪያ አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም