ለአገር ዘላቂ ሰላም መከበር የማስተማር ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን

95


ግንቦት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ልማት እንዲቀጥል ህብረተሰቡን የማስተማር ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በድሬዳዋ የኃይማኖት አባቶች፣የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ዑጋዞች አስታወቁ።

ዛሬ በድሬዳዋ የኃይማኖት አባቶች ፣የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና ዑጋዞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና በሰላም ላይ ውይይት አድርገዋል።

በድሬዳዋ ያለውን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትና ሰላምን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለህግ ማቅረብ እንደሚስፈልግ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው እንዳሉት፤በመላው አገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ፍቅር፣መተሳሰብና አንድነት እንዲሰፍን የኃይማኖት አባቶች ህብረተሰቡን የማስተማር ተግባራቸውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡

የኃይማኖት አባቶች ህዝብን በማስተማር ሰላምና ፍቅር እንዲጠናከር በተናጥልና በጋራ እያስተማሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

"አንዳንድ ጊዜ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮና ከህበረተሰቡ እሴት በሚቃረን መልኩ ህገ-ወጥ ተግባራት የሚፈፅሙ አካላትን መንግስት ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ ለህግ ማቅረብ አለበት" ብለዋል ፡፡

"ድሬዳዋ ዘመን የተሻገረ ህብረ-ብሔራዊ ፍቅርና አንድነትን ያነገበ ህዝብ ያለባት ከተማ ናት" ያሉት ደግሞ የአገር ሽማግሌ አቶ መሐመድ ሙሴ ናቸው፡፡

"ነዋሪዎቿ በዓላትንና ችግርን በጋራ የማሳለፍ እሴትን በማጠናከር፣ የውይይትና የምክክር ባህላችንን በማስቀጠል ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በመከላከል ወቅታዊ ክስተቶችን በጋራ መሻገር አለብን" ብለዋል፡፡

በተለይ ወጣቱ በማህበራዊ ሚዲያ አሉባልታ እንዳይሸነፍ ቤተሰብ የማስተማር ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የድሬዳዋ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢና የድሬዳዋ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ አብደላ በራርቲ "የኃይማኖት መሪዎች በየተቋሞቻቸው ለወጣቱ በሰላምና አንድነት ላይ ትኩረት አድርገው እያስተማሩ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

''ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር የለም፣ለሰላም እንጸልያለን፣የእምነት መሠረት ሰላም ነው፤ወጣቱ ለአገሩ ሰላምና ልማት ተግቶ መቆም አለበት" ሲሉ ገልጸዋል።

መንግሰትም የህዝብን ሰላም የሚያደፈርሱ ግለሰቦችን በፍጥነት ለህግ ማቅረብ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በድሬዳዋና በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚኖረው ማህበረሰብ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እንዲቆም ከመቼውም ጊዜ በላይ እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአፍረን ቀሎ አባገዳ አብዱረዛቅ አህመድ ናቸው።

"መንግስት ለማህበረሰብ እየፈጠረ ያለው የውይይት መድረክ ችግርን በጋራ ለማስወገድና የጋራ መግባባት ለመፍጠር የሚያግዝ በመሆኑ መጠናከር አለበት" ብለዋል፡፡

"በተለይ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ተገልጋዩን ለብሶት የሚዳርጉና ለአገር ሰላም መናጋት ምክንያት የሚሆኑ አመራሮችና ባለሞያዎችን በህግ ተጠያቂ በማድረግ ሀገራዊ ለውጡን ዳር ማድረስ ያስፈልጋል" ሲሉም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም