በኢትዮጵያ ውጤታማ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት የፖሊሲና አሰራር ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል

177

ግንቦት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ውጤታማ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት የፖሊሲና አሰራር ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ።

አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን፤ በጉባኤው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ የዘርፉ ምሁራን፣ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎችና በምስራቅ  አፍሪካ የሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡

ጉባኤውን ያዘጋጁት ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ መድህን ሰጪዎች ድርጅት፣ የተመሰከረላቸው ሂሳብ ባለሙያዎች ማህበር እና "አይ ካፒታል" የተሰኘ ኢንስቲትዩት በጋራ በመሆን ነው።  

በጉባኤው በዋናነት በቀጣናው ጠንካራ የፋይናንስ ዘርፍ ለመፍጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ፣ ቁጥጥርና አስተዳደር፣ የፋይናንስ አካታችነትና ልዩ የባንክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነው የመከረው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ የተሻለ የፋይናን ስርዓት መዘርጋት የሚያስችሉ የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የግሉን ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ገልጸው፤ የብድር አቅርቦት ማሻሻል እና የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ማስፋት ጨምሮ ሌሎች ማሻሻያዎች መከናወናቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

የለውጥ ስራዎቹ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል።

የአይ ካፒታል ኢንስቲትዩት መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ገመቹ ዋቅቶላ በበኩላቸው በጉባኤው በፋይናንስ ዘርፍ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ተቋማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ በጥናት የተደገፈ ውይይት እንደሚደረግ አንስተዋል።     

በኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ጠንካራና ተወዳዳሪ የግል ተቋማትን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በገጠር አካባቢዎች የባንክና ኢንሹራንስ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ለዚህ ደግሞ የዘርፉን ተቋማት ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው አገራት ልምድ መውሰድና በሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም