የሁሉም እምነት አባቶች ስለ ሰላም ጠንክረው እንዲሰብኩ ጥሪ ቀረበ

ጭሮ፤ ግንቦት 3/2014(ኢዜአ) የሁሉም እምነት አባቶች በቤተክርስቲያንና በመስጅድ ለህብረተሰቡ ስለ ሰላም ጠንክረው በመስበክ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ እምነት አባቶች፤ የሀገር  ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች በሀይማኖት ሽፋን በሚነሱ የሰላም መደፍረስ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ መክረዋል፡፡

የጭሮ ቅድስት ልደታ ማርያም ቤተክርስቲያን ስብከተ ወንጌል ኃላፊ ቀሲስ ማቲያስ ምንዳ  ችግር በሚፈጥሩ ጥቂት ጥፋተኞች ቤተ እምነቶች መፍረስና መቃጠል የለባቸውም ብለዋል፡፡

በስልጣን ላይ ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ወደ አንድነት የሚወስደውን መንገድ ማረጋገጥ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሀይማኖት አባት እኛም በየቤተእምነቶች  ሰላም እንዲከበር እናስተምራለን ብለዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች ሼህ አህመድ መሀመድ እንደገለጹት፤ የሀይማኖት አባቶች ወንድማማችነትን በማጠናከር ሰላማዊ የጋራ ሀገር የመገንባቱ ድርሻቸው ከፍተኛ ነው፡፡

አንዱ የሌላውን ሀይማኖት አክብሮ በኖረበት ሀገር ሀይማኖት የፀብ መነሻ ሊሆን እንደማይገባ ነው ያመለከቱት፡፡

ሼህ አህመድ፤ ሙስሊሙና  ክርስቲያኑ  ሁለቱም የአደምና የሀዋ ልጆች በመሆናቸው አንድነታቸውን ዛሬ መጥቶ የሚያደፈርስ አይኖርም ፤ ሰላማችንን ለመጠበቅ  ጠንክረን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ሼህ ሙሳ አብደላ በሰጡት አስተያየት፤ ሰላም የሰው ልጆች ህልውና መሰረት በመሆኑ ሁሉም የሰላምን ዋጋ ተረድቶ በጋራ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በየዘርፉ የሚገኙ አመራሮችም ሰላም ተጠብቆ የሚቀጥልበትን የመፍትሔ አቅጣጫ በመጠቆም ህብረተሰብንም ማንቃት ተቀዳሚ ስራቸው መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡

ሰላም አደፍራሾችንም ማውገዝና ወደ ሰላም እንዲመጡ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል ሼህ ሙሳ ፡፡

በሃይማኖት ሽፋን  ሰላም ሲያደፈርሱ የነበሩ አካላት እኛን አይወክሉም በፅኑ እናወግዘዋለን ያሉት ደግሞ  የቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ወንጌል ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ፍቅረዮሐንስ  ተሾመ ናቸው፡፡

የሰላም ባለቤት ህብረተሰቡ በመሆኑ  በየአካባቢው ያሉ አፈንጋጮችን በማጋለጥ ፣በማስተማር የተረጋጋ ሀገር መፍጠር ከሁሉም ይጠበቃል ሲሉም አክዋል፡፡

የሁሉም እምነት አባቶች በመስጅድና ቤተክርስቲያን  ስለ ሰላም  ጠንክረው በመስበክ የድርሻቸውን እንዲወጡ  አስተያየት ሰጪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ ኡመር፤ ሰላምን በየቤተ እምነቶች ማስተማርና ህብረተሰቡ ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር ማስተባበር እንዲችሉ  ከሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎቹ ጋር ከስምምነት ተደርሷል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢ የተከሰተው ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ የሰላም መደፍረስ በጭሮ ከተማ እንዳይደገም ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ  ከንቲባው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም