የደቡብ ክልል የብሔረሰብ ምክር ቤት የክልሉን ብሄር ብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ የያዙ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት አስረከበ

101

ግንቦት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል የብሔረሰብ ምክር ቤት የክልሉን ብሄር ብሔረሰቦች ባህል፣ቋንቋና ታሪክ የያዙ መጻህፍትን ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት አስረከበ።

“አንድ ሚሊዮን መጻህፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ ለአብርሆት ቤተ-መጻህፍት የተጀመረው የመጻህፍት ማሰባሰብ መርሃ- ግብር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ምክር ቤቱም ለዚሁ ጥሪ ምላሽ በመስጠት የክልሉን ብሄር ብሔረሰቦች ማንነት፣ ቋንቋ፣ባህልና ታሪክ የያዙ መጻህፍትን አበርክቷል።

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ገመቹ አሪቦ የክልሉን ብሄር ብሔረሰቦች ታሪክ የሰነዱና የግጭት አፈታት ዘዴን ጭምር ያካተቱ 200 መጻህፍትን ለቤተ-መጻህፍቱ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ለትምህርት፣ ለጥናትና ምርምር የሚያገለግሉና በውድ ዋጋ የተገዙ 60 ተጨማሪ መጻህፍትንም ማስረከባቸውን ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የተዘጋጁት መጻህፍት በክልሉ የሚገኝ ብሔረሰቦች ላይ ጥናት ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች እንደ ግብዓት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በሀገር ደረጃ የተጀመረው አንድ ሚሊዮን መጻህፍት የማሰባሰብ መርሃ-ግብር እንዲሳካ ክልሉ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የአብርሆት ቤተ-መጻህፍት ተጠሪ መስፍን ገዛኸኝ፤ ምክር ቤቱ ያበረከታቸው መጻህፍት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር በቀል እውቀት የተዘጋጁ፣ የትኛውም ገበያ ላይ የማይገኙ መጽሐፍት በመሆናቸው ለቤተ-መጻህፍቱ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው ምክር ቤቱ ላደረገው ልገሳ ምስጋና አቅርበዋል።

የሀረሪ ክልልም ቀደም ሲል የክልሉን ነዋሪዎች ባህል፣ ቋንቋ፣ ባህል አኗኗር የሰነዱ መጻህፍትን ማስረከቡን አስታውሰው ሌሎችም ልገሳ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

“አንድ ሚሊዮን መጻህፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ” በሚል እየተካሄደ ባለው የመፅሃፍት ማሰባሰብ ዘመቻ በርካታ ተቋማት፣ ግለሰቦችና ማህበራት እየለገሱ ሲሆን በግለሰቦች ደረጃ ብቻ በየቀኑ በአማካይ ከ500 እስከ 1 ሺህ መጻህፍት እየተለገሰ መሆኑ ታውቋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️