ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል

85

አዳማ፣ ግንቦት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዴንጋሞ እንደገለፁት፤ በውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጥራት ቁጥጥርና አስተዳደር ላይ ሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የተቆጣጣሪዎችን አቅም ለመገንባት እየተሰራ ይገኛል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በተቀመጠው ደረጃ መሰረት 69 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው፤ ባለፋት ዘጠኝ ወራት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል ሲሉ ገልጸዋል።

በፌዴራልና በክልሎች በርካታ የመጠጥና የመስኖ ፕሮጄክቶች ግንባታ እየተከናወኑ መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአንጻሩ የፕሮጀክቶች ግንባታ መዘግየትና ተጨማሪ ወጪ መጠየቅ፣ የጥራት ጉድለትና አገልግሎት ሳይሰጡ የመበላሸት ሁኔታዎች ይታያሉ ብለዋል።

መንግስት በውሃ መሰረተ ልማት የግንባታ ጥራት፣ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራዎችና የመስመር ዝርጋታዎችን ችግር ለመፍታት ከመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለፈ በዕውቀትና ክህሎት የበቁ ተቆጣጣሪ ሙያተኞች አቅም ግንባታ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ግንባታቸው ከተጠናቀቀው የውሃ ተቋማት መካከል በግንባታ ጥራት ጉድለትና ብልሽትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያት 20 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአሁኑ ወቅት የውሃ ተቋማት ቆጠራ ለማከናወን ማኑዋል እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም ከእንግሊዝ መንግስት በተሰጠ ድጋፍ ከተለያዩ ክልሎች የተወጣጡ ሰልጣኞች ዛሬ ተመርቀዋል ብለዋል።

በሚኒስቴሩ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የመጠጥ ውሃና ሳንቴሽን ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ሉሌ በበኩላቸው የውሃ ተቋማት ግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የመጠጥ ውሃ መሰረት ልማትና ሳንቴሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችሉ የውሃ ተቋማት ግንባታን ጨምሮ ሰባት መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በውሃ ሴክተር የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፉ ወሳኝ ሚና ያላቸው መመሪያ ከማዘጋጀት ባለፈ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጄክቶች የግንባታ ችግር ብቻ ሳይሆን ሰፊ የሆነ የክትትልና ቁጥጥር ውስንነትና የዕውቀት ማነስ ክፍተት በመኖሩ ዘላቂ የአቅም ግንባታ ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም