ድርጅቱ ለአፋር ክልል የአምቡላንስና ሥነ-ተዋልዶ ጤና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ

113

ግንቦት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ /ዩኤን ኤፍ ፒ ኤ/ ከዴንማርክ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ለአፋር ክልል የአምቡላንስ እና ሥነ ተዋልዶ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ጤና ተቋማት ለማጠናከር የሚውል ነው ተብሏል።

ድጋፉን የመንግሥታት ድርጅት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ሳራ ማሳሌ በጤና ሚኒስቴር የሴቶችና ሕጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም አስረክበዋል።

ዶክተር መሰረት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት በመውደማቸው ምክንያት እናቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ተጎጂ ሆነዋል።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎቶች ለማጠናከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የዛሬው ድጋፍም የዚህ አካል መሆኑን አብራርተዋል።

“ድጋፉ አንገብጋቢ የሆነው ለእናቶች፣ወጣቶች ሕጻናት ጤና አገልግሎት የሚውል በመሆኑ በእጅጉ ማመስገን እንፈልጋለን” ነው ያሉት።

የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጠይባ መሃመድ በበኩላቸው ድጋፉ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ለማቋቋም ይረዳል ብለዋል።

የመንግሥታት ድርጅት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ሳራ ማሳሌ በበኩላቸው ድርጅቱ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ለችግር የተጋለጡ ሥፍራዎችን ለይቷል።

ከእነዚህም አካባቢዎች መካከል አንዱ ለሆነው አፋር ክልል አምቡላንሶች፣የሥነ ተዋልዶ ጤናና የሴቶችን ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም ለአማራና ቤንሻንጉል ክልሎች ተጨማሪ አምቡላንሶችን ለመግዛትና ለማከፋፈል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️