ብሔራዊ ደም ባንክ የደም ክምችት እጥረት በማጋጠሙ ኀብረተሰቡ ደም በመለገስ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረበ

108

ግንቦት 3 /2014(ኢዜአ)  ብሔራዊ ደም ባንክ የደም ክምችት እጥረት በማጋጠሙ ኀብረተሰቡ ደም በመለገስ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቀረበ፡፡

የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ የመደበኛና የዕለት ተዕለት የደም ለጋሾች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በቂ የደም ክምችት እንዲኖር የመደበኛ ደም ለጋሾች ቁጥር መጨመር እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለዚህ ደግሞ የደም ልገሳ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊጎለብት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ በየ ሶስት ወሩ በቋሚነት ደም እንዲለግስ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

መደበኛ የደም ለጋሾች ቁጥርን ለማሳደግ ከተለያዩ ከትምህርት ቤቶች ፤ክበባት እና ከሌሎች  ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም በአሁኑ ወቅት የደም ክምችት እጥረት መከሰቱን ጠቅሰው፤ እጥረቱ በተለይ በ “ኦ ኔጌቲቭ” የደም አይነት ላይ የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በክርስቲያንና ሙስሊም ጾም ወቅት የለጋሾች ቁጥር በመቀነሱ ምክንያት ከፍተኛ የደም እጥረት መከሰቱን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ኀብረተሰቡ በስፋት ደም በመለገስ እጥረቱን ለመቅረፍ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ ሰዎች መካከል ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ብቻ ደም እንደሚለግሱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡