ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚመጥን ጠንካራ ሠራዊት እየተገነባ ነው - ጄነራል ጌታቸው ጉዲና

167

ግንቦት 3/ 2014(ኢዜአ) የአገርና የህዝብ መከታ የሆነ ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚመጥን ጠንካራ የአገር መከላከያ ሰራዊት እየተገነባ መሆኑን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጄነራል ጌታቸው ጉዲና ገለጹ።

የአገር መከላከያ ሠራዊት የህዝብ ወገንተኝነቱን አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ለማድረግ አዲስ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ጀነራል ጌታቸው ጉዲና ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሁላችንም የሆነችውን አገር መከታ ሆኖ የሚጠብቅ ኢትዮጵያን የሚመስል ጠንካራ ሰራዊት እየተገነባ ነው ብለዋል።

ሰራዊቱ ለፓርቲ፣ ለብሔር ወይም ለቡድን የወገነ ሳይሆን የህዝብን ጥቅም በማስቀደም ለአገር ሉዓላዊነትን የቆመ በህገ መንግስቱ የሚመራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በህወሓት መራሹ ኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን የሰራዊቱ አደረጃጀት የኢትዮጵያ መልክና ገጽታ እንዳልነበረው አስታውሰው አሸባሪው ህወሃት ስልጣኑን የሚጠብቁለትን አካላት መሰብሰብ ቀዳሚ ተግባሩ እንደነበር ገልጸዋል።

ይህ ቡድን እስከ 8ዐ በመቶ የሚሆነው የሰራዊቱ አመራርና ስታፍ ከአንድ አካባቢ በመጡ ሰዎች በማደራጀቱ በህዝባዊ ጫና ስልጣኑን ካጣ ወዲህ አደረጃጀቱን አገር ለማተራመስና ለማፍረስ ሴራው እንደተጠቀመበት ገልጸዋል።

ለዚህም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ክህደት ማረጋገጫ መሆኑን አስታውቀዋል።

ነገር ግን ሰራዊቱ ክህደት ተፈጽሞበት በህልውና ዘመቻና በዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ተጋድሎ ውስጥ ሆኖም ትልልቅ የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንና ሠራዊቱን ትክክለኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ተምሳሌት ለማድረግ ያልተቋረጠ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሰራዊቱ ከመላ ኢትዮጵያ በተውጣጡ ልጆች መደራጀቱን ተናግረው ይህም የእኔነት ስሜት እየፈጠረና ትክክለኛ ህዝባዊነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያውያን ለጋራ ደህንነታቸውና ሉአላዊነታቸው መጠበቅ አምነውና ፈቅደዉ የገነቡት የአገር ሉአላዊነት የመጨረሻው መሸሸጊያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም