ለአገር አንድነትና ለህዝብ ደህንነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች እውቅና መስጠት በርካታ ጀግኖችን ይፈጥራል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

230

ባህር ዳር፣ ግንቦት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአገር አንድነትና ለህዝብ ደህንነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች እውቅና መስጠትና ማወደስ በርካታ ጀግኖች ነገ እንዲፈጠሩ የሚያደርግ አኩሪ ባህል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

በባህር ዳር ከተማ "በህግ ማስከብር እና በህልውና ዘመቻ የተከፈለ መስዋዕትነት ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት" በሚል መሪ ቃል የእውቅናና ምስጋና ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስነ ስርዓቱ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ አገር ስትደፈር በአንድነት ተሰልፎ ለነጻነቱ እንደሚዋደቅ ከታሪክ መማር ይቻላል።

በዚህ ዘመንም አሸባሪው የህወሃት ቡድንን አገር ለማፍረስ በመንቀሳቀሱ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን፣ አጥንታቸውን፣ ጉልበታቸንውንና ሃብታቸውን ጭምር በመስጠት አገር ማኩራታቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ጀግኖቻችን በዚያ የሰሜን እዝ በአሸባሪው ቡድን በተጠቃበትና ወረራ በፈጸመበት የጨለማ ጊዜ ውስጥ ሆነው በከፈሉት መስዋዕትነት ለአገር አንድነት ብርሃን ያበሩ ናቸው ብለዋል።

ዛሬም ጠላቶቻችን በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በባህል ተከፋፍለዋል ብለው በማሰብ ወረራ ለመፈጸምና ለማጥቃት የሚያስቡ ሃይሎች ከአሸባሪው ህወሃት ሽንፈት መማር አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።

የአገራችንና የህዝባችን ሰላም ሲደፈርስ የሚደሰቱ ጠላቶቻችን ልክ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም መላው ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመሰለፍ የአገራቸውን ክብር በማስጠበቅ የአባቶቻቸውን አሻራ እንደሚያስቀጠሉ ማወቅ አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በህግ ማስከበሩና በህልውና ዘመቻው በርካታ ቁጥር ያላቸው የጸጥታ አካላት መስዋዕትነት ከፍለዋል ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ የዛሬው እውቅናና ሽልማት በመድረኩ ለተጠሩት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጀግኖች መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት ለማይቀረው የኢትዮጵያ ብልጽግናና የእድገት ጉዞ ሁሉም አካል በሚችለው ሁሉ በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

በእውቅናና የሽልማት ፕሮግራሙ ጀብዱ የፈጸሙ የጸጥታ ሃይሎች፣ መስዋዕት የከፈሉ ቤተሰቦች፣ ብቁ አመራር የሰጡ የሰራዊት አመራሮች፣ ባለሃብቶች፣ ሚዲያዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም