የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ባሕር ዳር ገቡ

159

ግንቦት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮችና ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የአማራ ክልል መንግሥት ባዘጋጀው በሕግ ማስከበርና በኅልውና ዘመቻ ለተሳተፉ የጸጥታ አካላት የዕውቅና መርኃ ግብር ላይ ለመሳተፍ ባሕር ዳር ገብተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር የጥፋት መንገዱን አክሽፈዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ባዘጋጀው የምሥጋናና የእውቅና መርኃ ግብር ለጸጥታ አካላት፣ ግለሰቦችና ተቋማት የዕውቅና መርኃ ግብሩ ትናንት ጀምሯል።

ዛሬም በሕግ ማስከበርና የኅልውና ዘመቻ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ልዩ ልዩ የጸጥታ አካላትና የክተት ጥሪ ተሳታፊ የሕዝብ ኀይል ዕውቅና ይሰጣል ሲል አሚኮ ዘግቧል።

ከሽብርተኛው ቡድን ጋር ሲፋለሙ በጀግንነት የተሰውትም ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በክብር ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በዘመቻው የተሳተፉ ተቋማት፣ ባለሐብቶች፣ የብዙኀን መገናኛዎችና ሌሎች አደረጃጀቶችም ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮችም ኢትዮጵያን ለማዳን በተደረገው ዘመቻ ላደረጉት አስተዋጽኦ ዕውቅና ይሰጣቸዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም