በፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች የሚወረወርብንን አፍራሽ አጀንዳ ለመመከት በአንድነት መቆም አለብን

96

ባህርዳር፣ ግንቦት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች የሚወረወርብንን አፍራሽ አጀንዳ ለመመከት በጠንካራ አንድነት መቆም አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

በʺበሕግ ማስከበርና በሕልውና ዘመቻው የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በዘመቻው የላቀ ሚና ላበረከቱ የፀጥታ አባላት እውቅናና የማዕረግ እድገት ዛሬ ተሰጥቷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በስነ እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ለመጣል የአገር ውስጥና የውጭ ሃይሎች እየሰሩ ይገኛሉ።

ጸረ-ኢትዮጵያ ሃይሎቹ በሃይማኖትና በብሔር አማካኝነት ኢትዮጵያውያንን ችግር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

በመሆኑም የተደቀነብንን አደጋ በመረዳትና ይህን አጀንዳ ለመመከት ህዝቡ አንድነቱን መጠበቅ አለበት ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የፈፀመው አገር ለማፍረስ በማለም መሆኑን አስታውሰው፤ በመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች የፀና ተጋድሎ ሴራው መክሸፉን ተናግረዋል።

“ጦርነትን የማንፈልገው የሚያስከትለውን ጉዳትና የሚያስከፍለውን ዋጋ ስለምንገነዘብ ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ አሸባሪው ቡድን ከጥፋት ድርጊቱ እንዲታቀብ አሳስበዋል።

የትግራይ ህዝብና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ ከጥፋቱ እንዲመለስ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተው፤ መንግስት ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት ሙሉ አቅምና ዝግጁነት እንዳለው ጠቁመዋል።

አሸባሪው የህውሃት ቡድን ሃገር ለማፍረስ የወጠነውን ሴራ በተደራጀ አግባብ በማክሸፍ የፀጥታ ሃይሉና ህዝብ ያበረከተው ሚና በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ናቸው።

የክልሉ የፀጥታ ሃይል ከፌዴራልና ሌሎች ክልሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር ወራሪውንና አሸባሪውን ህወሃት ድባቅ በመምታት ሴራውን ማክሸፍ እንደተቻለ አስታውሰዋል።

የዛሬው እውቅናና የማዕረግ እድገት መስጠት መርሃ ግብር የፀጥታ ሃይሉን ሞራል በማነሳሳት አሸባሪው ህውሃት ሊፈፅም ያቅደውን ዳግም ወረራ ለማምከን እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ቡድኑ ለዘመናት ከትግራይ ህዝብ ጋር ተዋልዶና ተዛምዶ በኖረው የአማራ ህዝብ ላይ ዘግናኝ ግፍና በደል መፈፀሙን ተናግረዋል።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው በህልውና ዘመቻው ተጋድሎ ለፈፀሙ ጀግኖችንና የጀግና ቤተሰቦችን እውቅና መሰጠቱ ሰራዊቱን ለላቀ ግዳጅ እንደሚያዘጋጀው ተናግረዋል።

የማእረግ እድገት የተሰጣቸው አመራሮችና ተዋጊዎች የተሰጣቸውን ግዳጅ በጥብቅ ዲስፕሊን በመምራትና በመፈፀም ለተገኘው ድል የላቀ አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸው ሲሉም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም