በማህበር ለተደራጁ 9 ሺህ 924 ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የእጣ ማውጣት ስነ ስርአት ተካሄደ

258

ደብረ ብርሃን፣ ግንቦት 2/2014 ( ኢዜአ) የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በማህበር ለተደራጁ 9 ሺህ 924 ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት ዛሬ የእጣ ማውጣት ስነ ስርአት አካሄደ ።

የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የቤት መስሪያ ቦታ ችግር ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ ነው።

በከተማው በህጋዊ መንገድ ለተደራጁ ህብረት ስራ ማህብራት የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዛሬው እለት በ431 ማህበራት ለተደራጁ 9 ሺህ 924 ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት የእጣ ማውጣት ስነ ስርአት መካሄዱን አመልከተዋል ።

በማህበራቱ ስር ለተደራጁ ነዋሪዎች ከሶስተኛ ወገን ነፃ የሆነ 343 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ለማህበራቱ ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓም ጀምሮ ቦታው ተሸንሽኖ ርክከብ እንደሚደረግ አመላክተዋል ።

ማህበራቱ የሚጠበቅባቸውን የቁጠባ ገንዘብ ገቢ ያደረጉ መሆናቸውን አመልክተው፤ “በከተማው ሌሎች ተደራጅተው እየተጠባበቁ ያሉ 202 ማህበራት የመንግስትን አሰራርን በመከተል የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል”‘ ብለዋል ።

የቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ከአራት ዓመት በላይ ተደራጅተው ሲጠባበቁ መቆየታቸውን የገለፁት ደግሞ አቶ ግዜው ፈጠነ ናቸው።

ዘግይቶም ቢሆን የእድሉ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸው መንግስት በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቦታ አቅርቦት ችግር ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።