ዳያስፖራው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባሻገር በኢንቨስትመንት የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ ተጠየቀ

167

ሐረር፣ ግንቦት 2/2014(ኢዜአ) ዳያስፖራው የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ከመገንባት ባሻገር በኢንቨስትመንት የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያሳድግ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ ኢድሪስ አስገነዘቡ ።

የዘንድሮው የሹዋል ኢድ በዓል ማጠቃለያ የሲምፖዚየምና ፓናል ውይይት ዛሬ በሐረር ከተማ ተካሂዷል።

ዶክተር መሐመድ በወቅቱ እንዳሉት ዳያስፖራው የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ከመገንባት ባሻገር በኢንቨስትመንት በመሳተፍ ለዕድገትና ልማቷ መሥራት አለበት።

ወደ ሐረሪ የመጡ ዳያስፖራዎች በክልሉ ኢንቨስትመንት በመሰማራት ዕድገቱን እንዲያፋጥኑ ጠይቀዋል።

”ሐረር ሀገር ሊያተርፍባት የሚችል የበርካታ ጥንታዊ ስልጣኔና ባህል ባለቤት ናት” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣”ባህሉን እንደጌጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለሀገር እድገትና ለህዝብ ትስስር ትልቅ መነሻ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።

ኤጀንሲያቸው የክልሉን ጥንታዊ ስልጣኔና ባህል ለሀገር ጥቅም ለማዋል በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በዓሉ ሐረር እንግዶቿን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ በማስተናገድ የእንግዳ ተቀባይነት እሴቷን ብሎም የፍቅር ሀገር መሆኗን በተግባር ያሳየችበት መሆኑን ዶክተር መሐመድ መስክረዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ የክልሉ ሕዝብ ዘመናት የተሸጋገሩና አኩሪ የባህል ቅርሶቹን በመንከባከብና በመጠበቅ ለትውልዶች እንዲያሸጋግር አሳስበዋል።

የሹዋል ኢድ በዓልን በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ማድረግ ለአካባቢው ብሎም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል ።

የታሪክ ተመራማሪው አቶ ኢብራሂም ሙሉሸዋ የሐረሪ የአለላ የባህል ስፌት (ጌይ ሞት) እንዳይጠፋ እየተደረገ ላለው እንቅስቃሴ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ባህሉን ለማቆየት በኮሌጅ ደረጃ ስልጠና መሰጠቱ ባህሉ ፋይዳው የላቀ እንደሆነ አመልክተዋል።

የባህል ስፌት ባለሙያዋ ወይዘሮ ኑሪያ አብዱላሂ በበኩላቸው በክልሉ ለባህላዊ ስፌቶች ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሴቶች ማህበር የተደራጁ 300 ሴቶች ስልጠና ወስደው በሙያው መሰማራታቸውን አስታውቀዋል።

”የሐረሪን ዕደ ጥበብ መስፋፋት ለኢትዮጵያ ያለው ፋይዳ የጎላ ነው ”ያሉት ደግሞ የሐረር ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ነቢላ ማህዲ ናቸው ።

በዓሉን በዓለም ቅርስነት ከማስመዝገብ ባሻገር፤ባህል አክባሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደፊት በሚከበሩት የሹዋል ኢድ በዓላት በመሳተፍ እሴቱን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስ የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ መነሻ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በሐረሪ ክልል ላለፉት ሦስት ቀናት የተከበረው የሹዋል ኢድ ክብረ በዓል ዛሬ ተጠናቋል።