ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

173

ሐዋሳ፣ ግንቦት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ቢሮ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በደን ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ያተኮሩ ተግባራትን በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን ዛሬ በሀዋሳው የኃይሌ ሪዞርት የተፈራረሙት የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ገመዶ ዳሌ እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ ናቸው።

በስምምነቱ ወቅት ዶክተር ገመዶ ዳሌ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ላለፉት 10 ዓመታት የኢትዮጵያን መንግሥት በተለያየ ደረጃ ሲደግፍ ቆይቷል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ስትራቴጂ ከመቅረጽ ጀምሮ የቴክኒክ፣ የፋይናንስ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ በመስጠት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አስታውሰዋል።

አሁንም ከኮሪያ መንግሥት በተገኘ የ9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ድጋፍ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ተቀርፆ በዚህ ዓመት ወደ ትግበራ መገባቱን አመላክተዋል።

ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር የተደረገው ይህ ስምምነትም የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ በአብዛኛው ፕሮጀክቱ በሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ በሆኑ ወረዳዎች የሚተገበር መሆኑን አስታውቀዋል።

በአለታ ወንዶ፣ ሻሸመኔ እና አርቤጎና ወረዳዎች ውስጥ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ የተጎዳ 13 ሺህ ሄክታር መሬት እንዲያገግምና ወደ ምርታማነት እንዲመለስ የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንዲሁም ያለውን የደን ሀብት መጠበቅና መንከባከብ፣ የህብረተሰቡን የኢኮኖሚና የገቢ ምንጭ አማራጮችን ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

ህብረተሰቡን በህግ ማእቀፍ በማደራጀት በውሃ ተፋሰሶች ተጠቃሚ እንዲሆን የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ይህንንም ስራ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ የተናገሩት ዶክተር ገመዶ፤ ኢትዮጵያ እየተከተለች ባለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲ ስኬታማነት ምላሽ የሚሰጡ ድጋፎች ይደረጋሉ ብለዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው በስምምነቱ መሠረት ዩኒቨርሲቲው ከአረንጓዴ ልማትና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ መፍትሄ የሚያመጡ የልማት ስራዎችን ያከናውናል ብለዋል።

ችግር ፈቺ የተለያዩ ጥናቶችና ምርምሮችም እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የደንና የአካባቢ ጥበቃ ስራ የሚያከናውን ኮሌጅ፣ የስምጥ ሸለቆ ሓይቆች ማዕከል እና በቂ የእጽዋት ላብራቶሪ ያለው መሆኑ ለፕሮጀክቱ ተመራጭ እንዳደረገው ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት የምርምርና የተግባር ስራዎችን፣ ሀብት የማሰባሰብ እንዲሁም  የምርምር ውጤቶችን በታዋቂ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች የሚታተምበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አብረን ለመስራት የጋራ ስምምነት አድርገናል ሲሉ አብራርተዋል።

በስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዐቱ ላይ የኮሪያ ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስስ ሄይ ጂዮንግ ጨምሮ የኢንስቲትይቱ እና የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም