በዞኑ ለድርቅ ተጎጂ ከፊል አርሶ አደሮች 412 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ ተደረገ

91

ጎባ፣ ግንቦት 2/2014 ዓ.ም (ኢዜአ)- በባሌ ዞን ለድርቅ ተጎጂ ከፊል አርሶ አደሮች 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ የተደረገው በዞኑ የወጣቶች አደረጃጀት  አማካኝነት ነው ።

የወጣት አደረጃጀቶቹ በዞኑ የድርቅ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 412 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ አድርገዋል ።

ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይ በግዢ  የቀረበው የስንዴ ምርጥ ዘር በሽታን በመቋቋምና ፈጥኖ በመድረስ የተሸለ ምርት የሚሰጥ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የዞኑ ወጣቶች ሊግ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ሁሴን ኢብራሂም ለኢዜአ እንደገለጹት የምርጥ ዘር ድጋፉ በዞኑ የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ ጉዳት የደረሰባቸው  ከፊል አርሶ አደሮች ከደረሰባቸው ችግር አገግመው  በዘላቂነት እንዲቋቋሙ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ነው።

 የዞኑ ወጣቶች አደረጃጀት አባላት ባሰባሰቡት 2 ሚሊዮን ብር መዋጮ ከኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ 412 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ግዥ ተፈጽሞ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሁሴን እንዳሉት መንግስት የድርቅ ተጎጂዎቹን ለማቋቋም እያደረገ የሚገኘው ጥረት እንዲሰምር የወጣት አደረጃጀቶችን በማቀናጀት የመደገፉ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ አማን በበኩላቸው የዞኑ ወጣቶች አደረጃጀት ላደረጉት ሰብዓዊ ድጋፍ በጽህፈት ቤቱና በተጎጂዎች ሥም አመስግነዋል፡፡

ድጋፉ በዝናብ እጥረት ሳቢያ በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ተጎጂ ከፊል አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ 2ኛ ዙር ልማት መሬታቸውን በማልማት ከደረሰባቸው ችግር እንዲያገግሙ ለማድረግ ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አብዲ እንዳሉት በዞኑ በአንደኛው ዙር የበጋ ወቅት ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እስከ አሁን ከ90 በመቶ በላይ ለማልማት መቻሉን አመልክተዋል፡፡

በባሌ ዞን የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 400 ሺህ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች እንዲሁም እንስሳት ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም