ዩኒቨርሲቲው ዝርያቸው የተሻሻለ ከ450 ሺህ በላይ የቡና ችግኞችን ለአርሶ አደሮች አሰራጨ

159

ዲላ፣  ግንቦት 2/2014 (ኢዜአ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ዝርያቸው የተሻሻለና የተሻለ ምርት የሚሰጡ ከ450 ሺህ በላይ የቡና ችግኞች ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ክብሩ አለሙ ለኢዜአ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በጌዴኦ ዞን በይርጋጨፌና ዲላ ዙሪያ እንዲሁም በምእራብ ጉጂ ዞን በአባያ ወረዳዎች ባቋቋማቸው አምስት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት የተዘጋጁ ከ450 ሺህ በላይ የተሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞችን  ለአርሶ አደሮች አሰራጭቷል ።

የቡና ችግኞቹ የተሰራጩት በወረዳዎቹ ለተመረጡና ለዘንድሮ ተከላ የሚሆን የማሳ ዝግጅት ላጠናቀቁ 650 አርሶ አደሮች መሆኑን ተናግረዋል ።

የቡና ችግኞቹ ምርት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የምስራች ምርት የሚሰጡና ከነባሩ የቡና ዝርያ በአማካኝ ከሚገኘው 5 ኩንታል ምርት በእጥፍ የመስጠት አቅም ያላቸው ዝርያዎች መሆናቸውን አመላክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለአርሶ አደሮች ካደረገው ከቡና ችግኝ ስርጭት በተጓዳኝ  በማሳ ዝግጅት፤ ተከላና እንክብካቤ ስራዎች የሙያ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊትም ለአርሶ አደሮች መሰል አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በመጭው አመት ለሚካሄድ ተከላ የሚሆኑ ችግኞች ለማዘጋጀት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

ዩኒቨርሲቲው በቡና ዘርፍ አገር አቀፍ የልዕቀት ማዕከል የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት  ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ስርፀት ዳይሬክተር ዶክተር ሃብታሙ ተመስገን ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉና በምርምር የተለዩ የቡና ችግኞችን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን በቡናና ምጣኔ ሀብት ልማት ላይ ያተኮሩ የድህረ ምረቃና የከፍተኛ ዲፕሎማ የትምህርት መርሃ ግብሮችን ከፍቶ የሰለጠነ የሰው ሃይል እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል።

“ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በሚያከናውናቸው ተግባራት ቡናን በሳይንሳዊ ምርምር የማልማት ስራ ከአርሶ አደሮች ማሳ ጋር በማስተሳሰር ከዘርፉ የሚገኙ ጥቅሞችን እያሰፋ ለመሄድ እገዛ እያደረገ ነው” ብለዋል።

ከአርሶ አደሮች ባለፈም በቡና ልማት የተሰማሩ ባለሃብቶችና የህብረት ስራ ማህበራትን አቅም በማጎልበት  ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የቡና ሽያጭ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ከፍ እንዲል የሚያስችል ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል ።

ዩኒቨርሲቲው  ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀራረብ በዘላቂነት ለመስራት  የሚያስችለውን የትግበራ ማዕቀፍ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል ።

በይርጋጨፌ ወረዳ ቡናና ሻና ቅመማ ቅመም ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበራ አሰፋ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሚያሰራጫቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኝ ዝርያዎች በአጭር ጊዜ ምርት በመስጠት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረጉን መሆናቸውን ተናግረዋል።

ችግኞቹ ያረጁ ቡናዎችን ነቅሎ በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባለፈ ነባር የቡና ዝርያዎች የመጀመሪያ ምርት ለመስጠት የሚፈጅባቸውን አምስት አመት ጊዜ በግማሽ የሚቀንሱ መሆናቸውንም ጨምረው  አስረድተዋል።

ከዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸውን ከ500 በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች መትከላቸውን  የተናገሩት ደግሞ በይርጋጨፌ ወረዳ ዶመርሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዘለቀ ሻሎ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በሚያደርግላቸው የተሻሻሉ የቡና ችግኝ እገዛ ምርታማነትን በማሳደግ ከቡና ልማት የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ተስፋ መሰነቃቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ከማሳ ዝግጅት አንስቶ እስከ ምርት መሰብሰብ ባለው ሂደት በሚያደርግላቸው  ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን አቅምና መነሳሳት እየፈጠረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በኮቾሬ ወረዳ ብሎያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምጁ ሳሊ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው 650 የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው  ችግኞች  ተረክበው መትከላቸውን ገልጸው የተደረገላቸው ድጋፍ ለቡና ችግኝ ግዠ ያወጡት የነበረን ከፍተኛ ወጭ ያስቀረላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።