ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በአንድነት በመቆም ሚናችንን ልናጎለብት ይገባል- ወጣቶች

166

ሀዋሳ ፤ ግንቦት 2/2014 (ኢዜአ) አባቶች ያቆዩትን አኩሪ ታሪክ ተንከባክቦ በመጠበቅ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በአንድነት በመቆም ሚናችንን ልናጎለብት ይገባል ሲሉ በሀዋሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ።
 

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመከላከል የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ወጣቶች በባለቤትነት መንፈስ መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸውም ተመልክቷል።

ከከተማዋ ወጣቶች መካከል በንግድ ስራ የተሰማራው ታምራት ተሰማ በሰጠው አስተያየት፤ ኢትዮጵያ የሰላም ባለቤት እንድትሆን ወጣቶች የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገረው።

ከዚህ አንፃር ጥቂቶች የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም በዘረጉት ስውር ሴራ ከመጠመድ ተቆጥበን የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ያለብንን  ድርብ ኃላፊነት መወጣት  አለብን ሲል ገልጿል።

እምነት የግጭት መንስዔ ሳይሆን የአንድነት፣የፍቅር፣የመተሳሰብና የመረዳዳት መገለጫ መሆኑን የጠቀሰው ወጣቱ፤ በተለይ የማህበረሰቡ አንቂዎች ግጭትን ከመቀስቀስና ከማባባስ ተቆጥበው የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ለማጠናከር ሊተጉ እንደሚገባ ተናግሯል።

በተለይ አባቶቻችን ያቆዩልንን አኩሪ ታሪክ ተንከባክበን በመጠበቅ ነገን ዛሬ በአግባቡ ስንሰራ  ሰላምን  በባለቤትነት እናረጋግጣለን  ብሏል ወጣት ታምራት።

ወጣቱ  ቴክኖሎጂን ለበጎ ተግባር በማዋል ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም በአንድነት መቆም እንዳለበት ተናግሯል።

ወጣት አብርሃም ብርሃኔ በበኩሉ ፤  በሀገሪቱ በእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸመው ድርጊት እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ገልፆ በተለይ ወጣቶች ከማናቸውም መጥፎ ተግባራት መራቅ አለብን ብሏል።

ወጣቶችን በገንዘብ በመደለል ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ  የሚያደርጉ ቡድኖች ሊኖሩ ስለሚችሉ የነዚህ የጥፋት  ሰለባ ከመሆን ራሱን መጠበቅም እንዲሁ።

የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመከላከል የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞና ዘላቂ ሰላም  ለማስቀጠል ወጣቶች  በባለቤትነት መንፈስ መሳተፍ ይጠበቅብናል ሲል አመልክቷል።

”የወጣቶች ሚና ለውጥ እንጂ፤ ነውጥ አለመሆኑን በስራችን ማረጋገጥ አለብን” የሚለው ወጣት አብርሃም በተለይ በኃይማኖት ሳንከፋፈል አንድ በሚያደርገን ሀሳብ ላይ እናተኩር ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች በጋራ የሚጋሯቸው ዕሴቶች መካከል አብሮነት፣ ሰብዓዊነት፣ ወንድማማችነትና ሰላም ዋነኞቹ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ወጣት ጉልታ ጀማል ነው።

ሆኖም የሀገራችን ጠላቶች ብሄር ከብሄር በማጋጨት ሀገር ለማፍረስ ያደረጉት ሙከራ አልሳካ ሲላቸው ኃይማኖትን አስታከው ዳግም ቢመጡም እንደማይሳካላቸው  ተናግሯል።  

ይልቁንም አንድነታችንን አጠናክረን ልናሳፍራቸውና ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ሚናችንን ልናጎለብት  ይገባል ብሏል።

”የኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ስሪት መለያየትን ሳይሆን መያያዝን፣ መገፋፋትን ሳይሆን፤ መደጋገፍ ነው ”ያለው አስተያየት ሰጪው፣ ወጣቶች ሰላምን ከሚያደፈርሱ ተግባራት ራሳችንን ማራቅ ይገባናል ነው ያለው።