በዘጠኝ ወራት ለ118 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል

111

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 02/2014(ኢዜአ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ118 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ገለጹ።

ኮሚሽነሯ በዘርፉ የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸምን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 3 ነጥብ 63 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ 2 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።

የእቅዱ አፈጻጸም 67 በመቶ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሯ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ18 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት አሳይተው ከተመለመሉ የውጭ ባለሃብቶች መካከል በዘጠኝ ወራት ለ203 ፕሮጀክቶች ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም ለ118 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው የእቅዱን 58 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል 68 የውጭ፣ 19 የአገር ውስጥ እንዲሁም 31 የሚሆኑት ደግሞ በጥምርታ ሲሆኑ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዙት የቻይና ባለሃብቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ፈቃድ ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል 65 በማኑፋክቸሪንግ፣ 50 በአገልግሎት እና ሦስት በግብርና ዘርፍ መሰማራታቸውንም ጠቅሰዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የአልባሳት፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች የወጪ ንግድ በዘጠኝ ወራት 223 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 156 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በማሳካት የእቅዱን 70 በመቶ ማከናወን ተችሏል።

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 21 በመቶ ወይም የ27 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ አለው ነው ያሉት።

ለእቅድ አፈጻጸሙ ዝቅ ማለት የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ፣ የኮሮናቫይረስ፣ የአፍሪካ አገራት ከቀረጥና ኮታ ነጻ ምርታቸውን ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርቡት አጎዋ) የገበያ እድል መሰረዝ ተጽዕኖ መፍጠሩ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት አይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ኮሚሽነሯ ጠቅሰዋል።

የሎጂስቲክስ ወጪ መናር፣ የአውሮፓ ገበያ መዳረሻቸው ለሆኑት ድርጅቶች የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እንዲሁም ሌሎችም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤክስፖርት ግብ መቀነስ ሌላው ምክንያት መሆናቸውንም ዘርዝረዋል።

በቀጣይ ኢንቨስተሮች ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ የሚሸጡባቸውንና ሌሎች አማራጭ ገበያዎችን የማማተር ሥራ እየተከናወነ ሲሆን የአውሮፓን ገበያ፣ ጃፓንና ቻይናን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል።

በቀጣይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የመሰረተ-ልማት፣ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ ሥራ ይጠብቀናል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት በተጀመሩ ፕሮጀክቶችም ከ57 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው በመግለጫቸው አመላክተዋል።