የኢትዮጵያን ነባራዊ ሃቅ በቅጡ በመረዳትና እውነታውን አምኖ በመቀበል በንግግርና መግባባት አገርን በፅኑ መሰረት ማስቀጠል አለብን

229

አዲስ አበባ ግንቦት 02/2014(ኢዜአ)  የኢትዮጵያን ነባራዊ ሃቅ በቅጡ በመረዳትና እውነታውን አምኖ በመቀበል በንግግርና መግባባት አገርን በፅኑ መሰረት ማስቀጠል አለብን ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዘጋጅነት "ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች" በሚል መሪ ኃሳብ ሕዝባዊ  የውይይት መድረክ በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በመድረኩ ተሳትፈዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ ግጭቶች በተለያዩ ምክንያቶች እንዲባባሱና እንዲስፋፉ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቂምና ጥላቻ እንዲሁም ቁርሾ ተወግዶ አብሮነትና የጋራ አገር መገንባትን አላማ አድርጎ መስራት የሁላችነም ሃላፊነት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።

ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሃቅ በቅጡ በመረዳት ስለኢትዮጵያ ሰላም፣ እድገት፣ አብሮነትና መቻቻል በጋራ መስራት ግድ ይለናል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ፈተናዎችን በጋራ ለመሻገር፣ እድሎችን ለመጠቀምና ተስፋዎቻችን ፍሬ እንዲኖራቸው ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው የፈተና ጊዜያት አንጸባራቂ ድሎች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ኢትዮጵያ ወደተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅብናል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በማስጠበቅ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የአገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ባለቤት መሆኗን ለዓለም ማስተዋወቅ  እንደሚገባም ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድ የአገሩን ሰላምና አንድነት የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሃመድ፤ ሌሎች አገሮችም የገጠሟቸውን ችግሮች የፈቱባቸው የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ የሚመቸውን በመምረጥ ከችግር ለመውጣት መስራት አለበን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያለፈቻቸውን ፈተናዎች፣ የተገኙ ድሎችና ወደ ፊት የተሻለ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የውይይት መድረኮች ወሳኝ መሆናቸውንም አመላክተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሬሳ፤ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታዎችና መገለጫዎች በአግባቡ በመረዳት በመተባበር፣ በመተጋገዝ፣ በመቻቻልና ተነጋግሮ ችግሮችን በመፍታት የአገርን ህልውና ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በሚኒስትር ማእረግ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ማስተባበሪያ ማእከል ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አብራሃም አለኽኝ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ለህዝቦቿ መኖሪያ የተመቸች አገር ለማድረግ በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም