ኢትዮ-ቴሌኮም የአገሪቱ የዲጂታል ሽግግር ዕውን እንዲሆን ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል

168

አዲስ አበባ ግንቦት 02/2014(ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችን በማቅረብ አገሪቱ ያቀደችው የዲጂታል ሽግግርን ዕውን ለማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኢትዮ-ቴሌኮም ገለጸ።

ኢትዮ-ቴሌኮም የ5ኛ ትውልድ (5 ጂ) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎትን በአዲስ አበባ በይፋ አስጀምሯል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ብዙ አድናቆት የተቸረው 5ኛ ትውልድ ኔትወርክ አገልግሎት ከአይን ርግብግቢት ያነሰ ወይም በአንድ ሚሊ ሰከንድ መረጃ መለዋወጥ ያስችላል ብለዋል።

የ5G የሞባይል ኔትወርክ በኢትዮጵያ በይፋ መጀመሩ የጤና አገልገሎትን ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማፋጠን እንዲሁም ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጂቢ የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ሲኖረው፣ በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ያገናኛል።

ይህም የአገርን ውስን ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም፣ የተሻለ፣ ምቹ፣ ፈጣንና ተወዳዳሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የሞባይል ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።

ለዜጎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት፤ ለኢንዱስትሪዎች መረጃዎችን በፍጥነት በመለዋወጥ ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችላል ነው ያሉት።

ዓለማችን የደረሰበት ይህ የመጨረሻ የገመድ አልባ ቴክኖሎጂ ለማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ሕክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

64 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ኢትዮ-ቴሌኮም የ5ጂ ቅድመ ገበያ አገልግሎትን በዋናው ኢትዮ ቴሌኮም መሥሪያ ቤት፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ አንድነት ፓርክ፣ በሻራተን ሆቴል አካባቢና በቸርችል ጉዳናን ያቀፈ 5ጂ ዞን ተብለዋል።

ኩባንያው የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ የቅድመ-ገበያ የሙከራ አገልግሎት በአዲስ አበባ ያስጀመረ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እስከ 150 ጣቢያዎች የመትከል ዕቅድ ተይዟል።

ኢትዮ-ቴሌኮም የ5ጂ ቴክኖሎጂን እውን ማድረጉ ተመራጭ የቴሌኮም ኦፕሬተር ለመሆን ከቀረጸው የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ጋር የተናበበ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕውን ለማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂ አማራጮችን በማቅረብ ጥረቱን እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ለቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዝርጋታዎችን ለማሳለጥ ሁሉም ወገን ትብብር እንዲያደርግ ገልጸዋል።

በማብሰሪያ መርሐግብር ላይ በ5 ጂ የሚንቀሳቀስ ዲጂታል ሮቦትም ለዕይታ በቅቷል።