በ68 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሰላምበር ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ህንጻ ተመረቀ

101

አርባ ምንጭ ግንቦት 02/2014 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን በ68 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የሰላምበር ኮንስትራክሽንና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ህንፃ ተመርቆ ለአገልግሎት ተዘጋጀ፡፡

 የኮሌጁ ህንጻ  በጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ትላንት ተመርቆ ለአገልግሎት ተዘጋጅቷል ።

ዋና አስተዳዳሪው  በወቅቱ እንዳሉት የኮሌጁ መገንባት መንግስት በፈጠራ ዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት በሰጠው ትኩረት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች  እንዲስፋፉ እየተደረገ ነው ።

በእለቱ የተመረቀውን ጨምሮ በዞኑ ውስጥ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ቁጥር ስምንት መድረሱን ጠቁመው  ኮሌጆቹ  ብቃት ያለው የሰው ሃይል እንዲያፈሩ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

በግንባታ ግብአቶች ንረት ምክንያት ተስተጓጉሎ የቆየው የኮሌጁ ህንጻ ግንባታ መንግስት በሰጠው ትኩረት ዘንድሮ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሯል " ያሉት ደግሞ  የሰላምበር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ማቴዎስ ማይዛ ናቸው።

የከተማው ህብረተሰብ ለኮሌጁ ግንባታ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸው ኮሌጁ አስፈላጊው ግብአቶች ተሟልተውለት አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ።

የኮሌጁ ዲን አቶ ድርጅት ድንበሩ በበኩላቸው የሰላምበር ኮንስትራክሽና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ በጥቂት የመማሪያ ክፍሎች ከ2008 ዓም ጀምሮ በተለያዩ ሙያዎች ተማሪዎችን ሲያሰለጥን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በአምስት የሙያ ዘርፎች ከደረጃ አንድ እስከ አራት 333 ተማሪዎችን በማስመረቅ ለአከባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የበኩሉን መወጣቱን አስረድተዋል፡፡

ከክልሉ በተመደበ 68 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው ኮሌጁ የመማሪያና የአስተዳደር ክፍሎች፣ የማምረቻ፣ የቤተመጻህፍትና  መሰብሰቡያ አዳራሽ ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሌጁ ዘንድሮ በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ በኮንስትራክሽን፣ በኤሌክትሪክ፣ በጋርመንትና በብረታ ብረት 681 ተማሪዎችን እያሰለጠነ እንደምገኝ አስታውቀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም