ለማህበረሰብ ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ዘርፎች ላይ የምርምር ስራዎች እየተካሄዱ ነው

124

ሆሳዕና ግንቦት 2/2014 (ኢዜአ) የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡና ለማህበረሰብ ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ ባላቸው ዘርፎች ላይ ያተኮሩ የምርምር ስራዎች እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ስምንተኛ ዙር ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ "ለህብረሰተብ ለውጥ የምርምር ስራዎችን ማጎልበት "በሚል መሪ ቃል አካሂዷል።

በዩኒቨርሲቲው  የምርምርና  ማህበረሰብ  አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፀደቀ ላምቦሬ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ በግብርና፣ በባህል ልማትና በቴክኖሎጂ ስርጸት ላይ ያተኮሩ 136 የጥናትና ምርምር ስራዎች እያከናወነ ነው።

ከነዚህም አዳዲስ ውጤቶች በማፍለቅ ለማህበረሰብ ለውጥ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብለው የተለዩ 56 ስራዎች በኮንፍረንሱ መቅረባቸውን አስረድተዋል።

የአካባቢውን ስነ ምህዳር  በመላመድና በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ አምስት አይነት የስንዴ ዝርያዎችን በምርምር በማረጋገጥ ውጤቱን ይፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ፀደቀ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባሉት ሰባት የምርምር ማዕከላት የአፈር ለምነትን በመጠበቅ የተሻለ ምርት የሚሰጡ ቡና፤ አዝርዕትና የእንሰሳት ምርጥ ዝርያዎችን ለማውጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም በምርምር የተረጋገጠና በሁለት ዓመታት ውስጥ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞችን ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አልሚዎች ማከፋፈሉን ምክትልፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡

"በተጨማሪም አዳዲስ የምርምር ውጤቶች እያፈለቀ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማሳለጥ እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በምርምር የሚገኙ ውጤቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የተናገሩት ዶክተር ፀደቀ፣ለአካባቢው ማህበረሰብ ችግሮች መፍትሄ ለሚያፈላልጉ ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።

በኮንፍንረሱ የተሳተፉት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአፈር ሳይንስና ኦርጋኒክ ኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አለሙ ለላጎ "ኮንፍረንሱ ለጥናትና ምርምር ስራዎቻቸው ተጨማሪ ዕውቀት አስገኝቶልኛል" ብለዋል።

"ምሁራን የምናውኗቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች  የሙያ ደረጃቸውን  ለማሳደግ ከዚያም  ሲያልፍ በአብዛኛው መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ አልፈው  ወደተግባር በመለወጥ  ማህበረሰቡን  ተጠቃሚ  ማድረግ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

በምሁራን የሚሰሩ የጥናትና የምርምር ስራዎች በድህነት ቅነሳና በዕውቀት ክፍተት ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኮንፍረንሱ የተሳተፉት ዶክተር ህዝቅኤል ፀዳ በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ የጥናትና የምርምር ስራዎች ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ ለሀገር ጠቀሜታ እንዳላቸው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሩ የምርምር ውጤቶች መሬት ላይ ተተግብረው የህዝብ የልማትና ሌሎች ጥያቄዎች እንዲመለሱ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

በመድረኩ በኢትዮጵያ የህንድና የኢንዶኔዥያ አምባሳደሮች ጨምሮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም