ባለስልጣኑ በአማራ ክልል በአሸባሪው ጉዳት ለደረሰባቸው ከተሞች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

125

ደሴ፤ ግንቦት 1/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው አራት ከተሞች ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

 ድጋፉን ዛሬ  በኮምቦልቻ ከተማ ተገኝተው  ያስረከበቡት የባለስልጣኑ  የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰርካለም ጌታቸው እንዳሉት ፤በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ ተቋማትን በጋራ መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡

ባለስልጣኑ በአማራ ክልል ኮምቦልቻ፣ ደሴ፤ ከሚሴና ወረኢሉ ከተሞች በአሸባሪው ለወደሙ የውሃ ተቋማትና የውሃ ጽህፈት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ ቁሳቁስ ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከተደረገው ድጋፍ መካከል ሞተር ብስክሌቶች፣ የውሃ ፓምፕ፣ ኮምፒዩተርና ፕሪንተር፣ ፓወር ኬብል እና ሌሎች የተለያዩ የውሀ አገልግሎት ቁስ ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።

ከተደረገው ድጋፍ  ከ8 ሚሊዮን ብር የሚበልጠው ቁሳቁስ የኮምቦልቻ ከተማ  መሆኑን አመላክተዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ኑረዲን ኢማም በበኩላቸው፤ ድጋፉ  የወደሙ የውሃ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

ለተደረገው ድጋፍም አመሰግነው፤ በሽብር ቡድን የወደሙ የውሃ ተቋማትን መልሶ በመጠገን ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።