የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ ለማህበራዊ ተቋማት ፈጣን አገልግሎትና ለኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት የላቀ ሚና አለው

ግንቦት 1/2014 (ኢዜአ)  የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ ለማህበራዊ ተቋማት ፈጣን አገልግሎትና ለኢንዱስትሪዎች ውጤታማነት የላቀ ሚና የሚኖረው መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናገሩ።

ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛ ትውልድ (5 ጂ) የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በአዲስ አበባ በይፋ አስጀምሯል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የ5G የሞባይል ኔትወርክ በኢትዮጵያ በይፋ መጀመሩ የጤና አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማፋጠን እንዲሁም ኢንዱስትሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት እስከ 10 ጂቢ የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ሲኖረው፣ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን (Ultra low latency) እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ ወደ 1 ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ እስከ 1 ሚሊዮን የሚደርሱ በርካታ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እርስ በርሳቸው ለማገናኘት የሚያስችል ዓለማችን የደረሰበት የመጨረሻ የገመድ አልባ ቴክኖሎጂ ነው ሲሉም አስረድተዋል።

ይሄው ፈጣን ቴክኖሎጂ የማምረቻ ፋብሪካዎች፣ ግብርና፣ ህክምና፣ ለመሳሰሉ ኢንዱስትሪዎች እጅግ የላቀ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኩባንያው የ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ የቅድመ-ገበያ የሙከራ አገልግሎት በአዲስ አበባ ያስጀመረ ሲሆን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች እስከ 150 ጣቢያዎች የመትከል እቅድ ተይዟል።

ኢትዮ ቴሌኮም የ5ጂ ቴክኖሎጂን እውን ማድረጉ ተመራጭ የቴሌኮም ኦፕሬተር ለመሆን ከቀረጸው የሦስት ዓመት የእድገት ስትራቴጂ ጋር የተናበበ ስለመሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም