የኢንተርፕራይዝ ልማት ለስራ እድል ፈጠራ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ አንቀሳቃሾች በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

113

ጋምቤላ ፤ ግንቦት 1/2014 (ኢዜአ) የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለኢኮኖሚያዊና ለስራ እድል ፈጠራ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ አንቀሳቃሾች በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጋምቤላ ክልል ከ400 ለሚበልጡ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች የአቅም ግንባታ ስልጠና በጋምቤላ ከተማ እየተሰጠ ነው።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ  በወቅቱ እንዳሉት፤ በጋምቤላ ክልል ሰፊ የመሬት፣ የውሃ ፣ የማዕድንና ሌሎች በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች ቢኖሩም በሚፈለገው ደረጃ ባለመልማታቻው ህዝቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል።

ሀብቱን ወደ ልማት በመለወጥ የክልሉን እድገት በማፋጠን ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ተሳትፎ ሊጠናክር ይገባል ነው ያሉት።

የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተጨማሪ ለስራ እድል ፈጠራ የጎላ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ውጤታማነት አንቀሳቃሾች በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዘርፉ በእውቀትና በቴክኖሎጂ ተደገፎ በምርት ጥራትና ብዛት ተወዳደሪ እንዲሆን በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እየተሰጠ ያለው የአቅም ግንባታ ስልጠና ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ምክትል ርዕስ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የኢትየጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በቪዲዮ ኮንፍረንስ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባንኩ  የመንግስትን የልማት እቅዶችን ውጤታማ ለማደረግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ በኢንቨስትመንት ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሃበቶች በሊዝና በፕሮጀክት ፋይናንስ ከሚሰጠው ድጋፍ በተጨማሪ ለዘርፉ መጠናከር የአቅም ግንባታ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመው የተጀመረው ስልጠናም  የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

ባንኩ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ቀደም ሲል የተበላሹ አሰራሮችን  በማስተካከል ትርፋማና በፈጣን የለውጥ መንገድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር  በጋምቤላ ጨምሮ በሀገሪቱ 20 ከተሞች በ35 የስልጠና ማዕከላት ለ34 ሺህ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቀሾች  ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ሰልጠኞቹ ከዛሬ ጀምሮ  በሚኖራቸው የአምስት ቀናት ቆይታ በሰው ሃብት አስተዳደር፣ በስራ ዝርዝር  እቅድ ዝግጅት፣ በፋይናንስና ሒሳብ አስተዳደር ጨምሮ በሌሎች የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ትምህርት እንደሚሰጣቸው ሪፖርተራችን ከጋምቤላ ዘግቧል።