ኢንተርፕራይዞች ከራሳቸው አልፈው አገር የሚጠቅሙ ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው

108

ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከራሳቸው አልፈው አገር የሚጠቅሙ ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት መስራት ያለባቸው መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።

በአገር አቀፍ ደረጃ 34 ሺህ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት ስልጠና በ20 የተለያዩ ከተሞች በዛሬው እለት ተጀምሯል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚካሄደውን ሶስተኛ ዙር አገር አቀፍ ስልጠና በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ በርካታ ዜጎች እውቀትንና የተፈጥሮ ሃብትን አመጣጥኖ ለመጠቀም ስልጠና ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከራሳቸው አልፈው አገር የሚጠቅሙ ተግባራት ላይ በልዩ ትኩረት መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

‘’ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መርህ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ንቅናቄ ለኢንተርፕራይዞች የስራ ዕድል ማስፋት ትልቅ አቅም አለው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው፤ ከ34 ሺህ በላይ ሰልጣኞችን የሚያሳትፈው ስልጠና በእውቀት እና ቴክኖሎጂ የተደገፈ የአምራች ዘርፍን ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በቂ ስልጠና ከተሰጠ በኋላ የመስሪያ እቃዎች ብድር በመስጠት የወጣቱን የስራ አጥነት ቁጥር ለመቀነስ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በአንደኛ እና ሁለተኛ ዙር ከ5 ሺህ 100 በላይ ወጣቶች ሰልጥነው 20 በመቶ የሚሆኑት የሚፈለግባቸውን አሟልተው የብድር ተጠቃሚ ሆነዋል ለዚህም 14 ቢሊዮን ብር ባንኩ አጽድቋል ብለዋል።

የዘንድሮውን አመት ካለፉት ሁለት ዙር ስልጠናዎች ለየት የሚያደርገው የተሳታፊዎች ስብጥር ያለውና  ካለፈው አመት በአስር እጥፍ ከፍ ማለት መቻሉንም ነው ዶክተር ዮሃንስ  የገለጹት።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ተገኝወርቅ ጌቱ፤ በበኩላቸው አገር አቀፍ ስልጠናው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረት የውጭ ምንዛሬን ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ከያሉበት ሆነው በዙም ባስተላለፉት መልእክት ለሰልጣኞች ከመስሪያ ቦታ ጀምሮ ሌሎች ድጋፎችንም ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።