” ሸዋል ኢድ” የተለያዩ ብሄረሰቦችን ባሳተፈ መልኩ መከበሩ በዓሉን ይበልጥ አድምቆታል -የበዓሉ ተሳታፊዎች

266

ሐረር ፤ ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዘንድሮው የ” ሸዋል ኢድ” በዓል ከኢድ እስከ ኢድ ፕሮግራም ውስጥ ተካቶ የተለያዩ እምነት ተከታዮችና ብሄረሰቦችን ባሳተፈ መልኩ መከበሩ ይበልጥ ደማቅ እንዳደረገው የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

የ” ሸዋል ኢድ” በዓል በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ፣ ከሌላው የሀገሪቱ አካባቢና ከውጭ  የመጡ እንግዶች በተገኙበት ትናንት ምሽት በድምቀት ተከብሯል ።

ክብረ በዓሉ በተለያዩ እምነት እና ባህል ባላቸው የኢትዮጵያ   ብሄር ብሄረሰቦች   አልባስና ጭፈራ ደምቆ መከበሩን ነው አስተያየታቸውን የሰጡ ታዳሚዎች የገለጹት።

በስነ-ሥርዓቱ ላይ የቀረቡት የተለያዩ ባህላዊ ትርኢቶችም በዓሉን ይበልጥ እንዳደመቀው ተመልክቷል።

ታዳሚዎቹ እንዳሉት፤ የዘንድሮው ሸዋል ኢድ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያለው ህዝብ የተሳተፈበትና የጋራ በዓል ሆኖ በድምቀት ነው የተከበረው።

ከካናዳ  የመጡት  አቶ ካሊድ አብዱልዋሲ  በሰጡት አስተያየት፤  በበዓሉ ለመሳተፍ መጥተው  ባዩት ዝግጅት  መደሰታቸውን  ገልጸዋል።

የሸዋል ኢድ በዓል በሐረሪ  ማህበረሰብ ዘንድ ብቻ ይከበር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ካሊድ፤ ዘንድሮ ግን ከቀድሞ በተለየ በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ታጅቦ  መከበሩ ይበልጥ ደማቅ እንዳደረገው ተናግረዋል።

ከስድስት ወራት በፊት ወደ ሀገር ቤት መጥተው እንደነበር በማስታወስ ፤ የበዓሉን ዝግጅት በመስማታቸው ተመልሰው መምጣታቸውን ደስተኛ ሆነው እንዳሳለፉ አስረድተዋል። 

ወይዘሮ ኢንቲሳር ሙክታር በበኩላቸው፤ በዓሉ የተለያዩ ብሄር ብህረሰቦች ተሳትፈውበት የጋራ  መሆኑ ይበልጥ ድምቀትን እንዳላበሰው ተናግረዋል። 

ሸዋል ኢድ  በሐረሪ ማህበረሰብ ዘንድ ለየት ያለ በዓል መሆኑን  የገለለጸችው ደግሞ ወይዘሪት ሳሚት መሃመድ ናት፡፡

በዓሉን ከተለያየ እምነት ተከታዮችና ብሄረሰቦች ጋር   በጋራ ማክበራቸው የዘንድሮው ለየት እንደሚያደረግው ተናግራለች ፡፡ 

ጓደኞቿን በማጀብ በበዓሉ ላይ እንደተገኙ የተናገሩት  ወይዘሮ ቤዛዊት ተሾመ በበኩላቸው፤ ሐረር ላይ በዓሉን  በአንድነትና በውንድማማችነት መንፈስ ተደስተው ማሳለፋቸውን ነው የገለጹት ፡፡

ወይዘሮ ኢማን መሃመድ ፤ በዓሉን ከሁሉም ጋር   በጋራ እንዳከበሩ ጠቅሰው፤  እንዲህ ዓይነት ቱባ ባህሎችን ለትውልድ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።