በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው የህብረተሰቡን ችግር መፍታት አለባቸው

164

ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው የህብረተሰቡን ችግር መፍታት አለባቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ምርምሮችን የሚያቀርብበትን የ2022 የምርምር ሣምንት መርሃ-ግብር እያካሄደ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የምርምር ሳምንት መርሃ-ግብር ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን ዘንድሮም ” የልህቀት ማእከሎች የለውጥ መሪዎች” በሚል መሪ ሃሳብ ማክበር ጀምሯል፡፡

መርሃ-ግብሩ በዩኒቨርሲቲው የሚደረጉ ምርምሮች ለህዝብ የሚቀርቡበት ከመሆኑም ባሻገር ምርምሩን፣ አንባቢዎችን እና ቀጣሪዎችንም ጭምር የሚያገናኝ መድረክ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው የህብረተሰቡን ችግር መፍታት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በዚህም የዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ውጤቶች ኢንዱስትሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች በእውቀት ላይ ተመስርተው ጥቅም ላይ እንዲያውሏቸው መሆን አለበት ሲሉ ጠቁመዋል።

በሳይንስና በምርምር የተደገፈ እድገት ለማምጣት እንዲያስችልም ዩኒቨርሲቲዎች፣ የመንግስት እና የግል ሴክተሮችም በቅንጅት መስራት አለባቸው ብለዋል።

የአርማውር ሃንሰን የምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር  ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤ ምርምር በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ አህጉርም ከአጀንዳ 2063 ጋር በእጅጉ የተያያዘ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ይህም ከታቀዱ የልማት አቅጣጫዎች ጋር ተጣጥሞ የበለጸገች አህጉር ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረትም በተለይም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክፍተቶችን ለመሙላት ምርምሮች አስፈላጊ እንደሆኑ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በያዘችው የአስር ዓመት እቅድ መሰረት በተለይም በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን ልማት፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ልማት ዘርፉ ምርምሮች አስፈላጊ እንደመሆናቸው ምርምሮች ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉ ናቸውም ነው ያሉት።

የምርምር ሳምንቱ በሁሉም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካምፓሶች ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት የሚካሄድ  ይሆናል።

በ10 ዓመቱ የዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ እቅድ ተቋሙን ከአፍሪካ የምርምር ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡