የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተለይም ለሴቶች፣ አርሶ አደሮችና አካል ጉዳተኞች በልዩ ትኩረት ይሰራል

134

ገንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በተለይም ለሴቶች፣ አርሶ አደሮችና አካል ጉዳተኞች በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ቴሌኮም ህብረት (ITU) ጋር በመተባበር ሚኒስቴሩ ያቋቋመው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማእከላት ይፋ ሆነዋል።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ኋላፊ ዶክተር አብዮት ባዩ፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትን ለማስፋት በዘርፉ የሚሰሩ ማዕከላትን ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።

በሚኒስቴሩና ዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ ቴሌኮም ህብረት ጋር በመተባበር ማእከላቱ የተቋቋሙ ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዲጂታል ክህሎት ተደራሽ ማድረግን ዓላማው አድርጎ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን የማስፋትና ስልጠናዎችን የማካሄድ ስራም በዋነኝነት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የቴክኖሎጂ ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት ለሴቶች፣ ለአርሶ አደሮችና አካል ጉዳተኞች ክህሎት የማጎልበት ስራ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማእከላቱ የተቋቋሙት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የወጣት ማእከላትን መሰረት አድርገው መሆኑም ታውቋል።

የድጅታል ማእከላቱ መቋቋም በ2030 ኢትዮጵያ ለምታሳካው ”የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ” እቅድ ስኬት የጎላ ሚና እንዳላቸው ዶክተር አብዮት ገልጸዋል።

የመረሃ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፤ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ለማሳለጥ የቴክኖሎጂ መስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማእከላት እውን መሆናቸው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንዛቤው ያደገ እና የተሻለች አገር ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ታምኖበት ነው ብለዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት የስራ እድል ፈጠራን ለማሳደግም አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

መረሃ ግብሩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የቴክኖሎጂውን ይዘት በሚመከት ገለጻና ውይይት የሚካሄድ ይሆናል።