በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና ይኖረዋል--የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና አገራት ምሁራን

95

ግንቦት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና አገራት ምሁራን ገለጹ።

በኢትዮጵያ ለረዥም ዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችና አለመግባባቶች ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት አገር በመገንባት ረገድ እክል ሲፈጥሩ ቆይተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መንግሥት አለመግባባቶችን አሳታፊ በሆነ አገራዊ ምክክር ለመፍታት ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑም አሁን ላይ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን መጥቀሱ ይታወቃል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና አገራት ምሁራን እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ለቀጠናው ሰላም ፋይዳው የጎላ ነው፡፡

በኤርትራ የስትራቴጂክ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ ዶክተር ፍቅረእየሱስ አምሃጺዮን ኢትዮጵያ ለቀጠናው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ወሳኝ አገር መሆኗን አንስተው፤ ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት መወሰናቸው ለቀጠናው ሰላም አዎንታዊ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ከቀጠናው ባለፈ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት መስፈንም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

ኤርትራ እንደ ጎረቤት አገር የኢትዮጵያን ሰላም እንደምትሻ ጠቅሰው፤ የአገራዊ ምክክሩ ተሳታፊዎች በሰለጠነ መንገድ በመወያየት የጋራ መግባባት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የፌደራሊዝምና ጸጥታ ጉዳዮች ትንተና ተቋም ሊቀመንበርና የቀድሞው የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር ጄነራል ዳይሬክተር ዶክተር ሶንኮር ጌይሬ በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ቀንድ ያለው የጸጥታ ችግር ቀጠናው በምጣኔ ሃብት እንዳያድግ አድርጎታል ብለዋል።

ላለፉት አሥርት ዓመታት ለጸጥታ መደፍረስ ምክንያት በመሆን ቀጠናውን ወደ ኋላ ያስቀሩትን ችግሮች   በውይይት በመፍታት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ችግሮችን በአካታች አገራዊ ምክክር ለመፍታት የጀመረችው ሂደት ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለፈው ላይ በመምክርና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ራዕይ በመያዝ ወደ አንድነት ከመጡ ምክክሩ ለአፍሪካ ቀንድ አዲስ ራዕይ ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።  

ኢትዮጵያና ሶማሌ የጋራ ድንበር የሚጋሩ፣ ወንድማማችና እህትማማች ህዝብ በመሆናቸው ለምክክሩ ውጤታማነት የሚጠበቅባቸውን  ድጋፍ እንደሚያደርጉም ዶክተር ሶንኮር ጌይሬ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም