በብሔርና በኃይማኖት ሽፋን ሊከፋፍሉን የሚሞክሩ ኃይሎችን ሴራ ማክሸፍ አለብን-ምሁራን

169

ዲላ ግንቦት 01/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በብሔርና በኃይማኖት ሽፋን ሊከፋፍሉን የሚሞክሩ ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ አንድነታችን ማስጠበቅ እንደሚገባ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስገነዘቡ።

የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ለኢዜአ እንደገለጹት ሀገር ለማፈራረስ በውስጥና በውጭ ኃይሎች እየተካሄደ ያለውን የተቀናጀ እንቅስቃሴ ለመግታት ለዘመናት የዘለቀውን አብሮነትና አንድነት ማጠናከር ይገባል።

መምህር ሄኖክ ንጉሤ የብሔር፣ የኃይማኖት፣ የቋንቋና የአስተሳሰብ ብዝሃነት የሰው ልጆች መገለጫ ብቻ ሳይሆን የምድራችንን ፀጋና ሀብት ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያም ብዝሃነትን እያስተናገደች አንድነቷን በማስጠበቅ ለሌሎች ሀገሮች ምሳሌ የሆነች ሀገር መሆኗ አመልክተዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ሀገሪቱ በዘመናት ሂደት፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ካካበተቻቸው እሴቶች በተጻራሪው የግጭትና የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ሲሞከር እየተስተዋለ ነው ብለዋል።

የኃይማኖትና የብሔር ብዝሃነትን ሽፋን በማድረግ የሚታዩ አንዳንድ አዝማሚያዎች ፈጥነው መታረም እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

መምህር ሄኖክ አክለውም በተለይ ወጣቶች ብዝሃነት ፀጋና ዘመናዊነት መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብትና ያለችበት ቀጠና የውጭ ሃገራት ፍላጎት የትኩረት ማዕከል እንድትሆን ማድረጉን መምህር ሄኖክ አስረድተዋል።

ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ህዝቦቿን ለመከፋፈል የሚደረጉ ሙከራዎች የሚቆሙትም ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር እንደሆነም አስገንዝበዋል።

መንግሥትም በኃይማኖትና ብሔር ሽፋን የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የሚሰሩ የግጭት ጠማቂዎችን ለይቶ የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ብለዋል።

በኃይማኖት ሽፋን የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ለማንጸባረቅ በቅርቡ የተደረገው ሙከራ ሀገሪቷን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የመክተት ሴራ አካል መሆኑን የዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ጥናቶች ኮሌጅ የዓለም አቀፍ ህግ መምህር አማኑኤል ታደሰ ገልጸዋል።

ሙከራዎቹ በኃይማኖት ሽፋን ፅንፈኝነትን በማንገስ የራስ ድብቅ የፖለቲካ ግብን ለማሳካት የታለሙ እንደሆኑም አስረድተዋል።

መንግሥት በሽብርተኝነትና በፅንፈኝነት ስም የሚደረግ እንቅስቃሴ በመከታተል የፋይናንስ ምንጮችን ማድረቅና የራሱንም መዋቅሮች መፈተሽ ይገባዋልም ብለዋል።

ህዝብና መንግሥት የኃይማኖት ፅንፈኝነት በቅንጅት መታገል ያስፈልጋል ያሉት መምህር አማኑኤል

ለዘመናት የዘለቀውን አብሮነት እሴት ለመሸርሸር የሚጥሩ አካላትን በማጋለጥ ሴራውን ማክሸፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም