የጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን በመቀነሱ የስራ ሠዓት ለውጥ ተደረገ

72

ጋምቤላ ፤ ግንቦት 1/2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን እየቀነሰ በመምጣቱ የመንግስት የሰራ ሠዓት ወደ መደበኛው መመለሱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽፍት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፒተር ሆው ለኢዜአ እንደገለጹት የሙቀት መጠን እየቀነሰ በመምጣቱና ለስራ ምቹ በመሆኑ ከዛሬ ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ቀድሞው የክልሉ የመንግስት ስራ ሠዓት እንዲመለስ ተደርጓል።

ላለፉት ሶስት ወራት ከጧቱ አንድ ሠዓት እስከ አምስት ሠዓት ተኩል የነበረው ከአንድ ሠዓት እስከ ስድስት ሠዓት ተኩል ፤ከሠዓት በኋላ ከአስር ሠዓት እስከ አስራ ሁለት ሠዓት ተኩል የነበረው ከዘጠኝ ሠዓት እስከ አስራ አንድ ሠዓት ተኩል ሆኖ ወደ ቀድሞው  መመለሱን ገልጸዋል።

የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች በቀድሞው መደበኛ ሠዓት ወደ ቢሮ በመግባት ሥራቸውን  እንዲያከናውኑ ኃላፊው አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ሜትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ዓለሙ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ አማካይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 31 ድግሪ ሰልሸስ ፤የሌሊቱ የመቀት መጠን ደግሞ 17 ዲግሪ ሰልሸስ ሆኗል።

ባለፉት ሶስት ወራት የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 42 ነጥብ 5፤ የሌሊቱ ደግሞ 26 ዲግሪ ሰልሸየስ ደርሶ እንደነበርም አስታውሰዋል።