ኢቢሲ በኢትዮጵያና በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሀን ተቋም ሆኖ እንዲወጣ እየተሰራ ነው -አቶ ፍስሃ ይታገሱ

99

ሐረር ሚያዚያ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በኢትዮጵያና በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሀን ተቋም ሆኖ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ አስታወቁ ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬሽን በምስራቁ አገሪቱ ክፍል ተደራሽነቱን ለማስፋት በሐረር ከተማ ያስገነባውን የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስቱዲዮ ዛሬ አስመርቋል ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ   የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፤ የኢትዮዽያ ብሮድካስቲንግ ኮርፕሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱና ሌሎች  የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች  ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍስሃ ይታገሱ  በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት ኢቢሲ በኢትዮጵያና በቀጠናው ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሀን ተቋም  ሆኖ እንዲወጣ እየተሰራ ነው ።

የሬዲዮና ቴሌቪዥን ስርጭቱን ተወዳጅና ተደራሽ ማድረግም ሌላው ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

”የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስቱዲዮዎችን ወቅቱን በጠበቀ  ቴክኖሎጂ በመገንባት  ይበልጥ ወደ ህዝብ እንድንቀርብ ያደርገናል፣ የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆነን እንድንዘልቅም ያግዘናል” ብለዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ሀረር ቅርንጫፍ ዳግም መከፈቱ ዘላቂ ሰላም፣ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ አስተዋጾ አለው” ብለዋል ።

የህዝብ ለህዝብ ትስስርና አንድነትን ለማጠናከር በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት የራሱን አስተዋጾ  የሚያበረክት እንደሆነም አመልክተዋል ።

የክልሉ  መንግስት በጣቢያው ዳግም መከፈት በትኩረትና በቅርበት ሲከታተልና አቅም የፈቀደውን ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ጠቁመው  በቀጣይም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የስቱዲዮ ግንባታው የአካባቢውን ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዜና እና ፕሮግራሞችን ለታዳሚ ለማድረስ እንደሚያስችል  በስነ ስርአቱ ላይ ተመላክቷል።

የኢትዮዽያ ሬድዮ ለምስራቁ አገሪቱ ክፍል ህዝብ ተደራሽነት ማዕከሉን ሐረር ከተማ ያደረገ ስርጭት በጥቅምት ወር 1965 ዓም የጀመረ ሲሆን ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ መቆየቱ ተገልፇል።

በአካባቢው ማህበረሰብ ቋንቋ የሬድዮ ስርጭት መጀመሩም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል።