ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ከግንቦት ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ መሰጠት ይጀምራል

122

ሚያዚያ 30/2014/ኢዜአ/ ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ከግንቦት ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች መሰጠት እንደሚጀምር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻና የዘጠኝ ወር የመደበኛ ክትባት አፈጻጸምን በሚመለከት ከክልልና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደር  ጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ግምገማ አካሂዷል፡፡

በግምገማ መድረኩ የክልሎችና የከተማ አስተዳደር የሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 ክትባት እና የመደበኛ ክትባት አፈጻጸማቸውን አቅርበዋል፡፡

በኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ ወቅት የነበሩ ጠንካራ ጎኖችና መስተካከል የሚገባቸው ነጥቦች ተለይተው ተገምግመዋል፡፡

በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች ክትባት ተደራሽ በማድረግ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት በጥንካሬ የተገመገሙ ሲሆን፤ በበጀት አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ክፍተቶች መታረም እንዳለባቸውም ተነስቷለ፡፡

የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተለይ ሁለተኛው ዙር የኮቪድ-19 ዘመቻ እንደ አገር በርካታ ጠንካራ ጎኖች የታዩበት ነበር ብለዋል፡፡

በታህሳስ ወር ከተካሄደው የመጀመሪው ዙር ክትባት ጥሩ ተሞክሮዎችን በመውሰድ በሁለተኛው ዙር ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ ደግሞ በግንቦት ወር መጨረሻ ሳምንት ላይ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች መሰጠት እንደሚጀምር የገለጹት ዶክተር ደረጀ፤ 25 ሚሊየን ዶዝ (መጠን) ክትባት ለማሰራጨት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ምን አይነት የኮቪድ ዝርያ ሊከሰት እንደሚችል ስለማይታወቅ ከትባት መውሰድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የሦስተኛው ዙር ክትባት ዘመቻ  የህብረተሰቡን በሽታ የመከላከል አቅም ከማሳደግ አኳያ ሚናው የጎላ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በጤና ሚኒስቴር በእናቶችና ህጻናት የጤናና ሥርዓተ-ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም ናቸው፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የኮቪድ-19 ክትባት መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ውስጥ 21 ሚሊዮን የሚሆኑት ክትባቱን ሙሉ በሙሉ የወሰዱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል እንደ አገር በመደበኛ ክትባት አሰጣጥ  ላይ የተሻለ አፈጻጸም መኖሩንም ነው ሚኒስትር ድኤታው ዶክተር ደረጀ የተናገሩት፡፡

“ክትባት ለልጆቻችን የምንሰጠው ትልቁ ስጦታ ነው” ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለይ በኩፍኝ ክትባት አሰጣጥ ላይ የታየው ክፍተት መታረም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በክልሎች መደበኛ ክትባትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ጤና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ እስከ መጋቢት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ  በአገር አቀፍ ደረጃ “ፔንታ 1” እና “ፔንታ 3” የተሰኙ የትክትክ፣ኢንፍሎይንዛና የጉበት በሽታ ክትባቶች ከ90 በመቶ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህም ውስጥ “ፔንታ- 1” የተሰኘው ክትባት አፈጻጸም 97 በመቶ መሆኑም ነው በመድረኩ የተገለጸው፡፡

“ኤም ሲቪ-2” የተሰኘው የኩፍኝ ክትባት አፈጻጸም ደግሞ 70 በመቶ ሲሆን፤ በቀጣይ ክትባቱን በስፋት ተደራሽ ማድረግ ላይ በትኩረት እንዲሰራ በመድረኩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡