የዳያስፖራ አባላት በተደራጀ አግባብ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም እንዲያስጠብቁ ጥሪ ቀረበ

152

ጅግጅጋ ሚያዝያ 30/2014 (ኢዜአ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በተደራጀ አግባብ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስጠብቁ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሃሺ ጥሪ አቀረቡ ።

"አገረ መንግስት ግንባታና የዲያስፖራ ሚና" በሚል  መርህ "ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት "ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ለመጡ  የዳያስፖራ አባላት በጅግጅጋ  የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ተጠናቋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሃሺ በውይይቱ ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት ዲያስፖራ አባላት በተደራጀ አግባብ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን  መልካም ገፅታ ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል።

"በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የምትገኙ የዳያስፖራ አባላት ብሄርና ሀይማኖት ሳይገድባችሁ በተደራጀ አግባብ በእንድነት በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም  ለማስጠበቅ መትጋት ይጠበቅባችኋል " ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል ።

"የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም  ለማስከበር ድምጻችሁን  በጉልህ ልታሰሙ ይገባል " ሲሉም አክለዋል   ።

የዳያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ዘርፍ  በመሳተፍ፣ ለሰላምና ለማህበራዊ ዕድገት ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ   ጠይቀዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ዳያስፖራው የሚያከናውናቸውን የልማት ተግባራት  ለመደገፍና አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ  ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ የዳያስፖራ አባላት  በሚኖሩበት ሀገር ያገኙትን  ልምድና እውቀት በመጠቀም በኢትዮጵያ በጸኑ መሰረት ላይ የተገነባ ሀገረ መንግስት መተግበር እንዲቻል አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

"ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ ሊካሄድ የታቀደው ሀገራዊ ምክክር መድረክ  ሂደት እየተጠናከረ ሲሄድ በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶች ይወገዳሉ" ያሉት ዶክተር መሀመድ ለመድረኩ ተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበዋል።

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር በሺር አብዱላሂ በበኩላቸው   የሰዎች ከሀገር ወደ ሀገር የመንቀሳቀስ ሁኔታ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአሉታዊ መልኩ ይታይ እንደነበር አስታውሰው፣ "አሁን ላይ ዳያስፖራው ለሀገሪቱ  ዕድገት አንድ የልማት አማራጭ እየሆነ መምጣቱ ግንዛቤ ተወስዷል" ብለዋል።

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንት፣ በእውቅትና ክህሎት ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ በመላክ  እያበረከተ ያለው አስተዋጾ ጠንካራ እንዲሆን የውይይት መድረኮች ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

በዓሉን ለመታደም ከሰኡዲ አረቢያ ጂዳ ከተማ የመጡ አቶ ሁሴን ሽፋ ሳሊያ ወደ ሚኖሩበት ሀገር ሲመለሱ ኢትዮጵያን  በተሻለ ሁኔታ ለማስተዋወቅ አቅም የሚሆናቸውን ጠቃሚ ግብዓት ከመድረኩ ማግኘታቸውን ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም