የአሸባሪውን ህወሃት ክፉ ህልም የምናመክነው ያወደማቸውን ተቋማት በተሻለ ደረጃ ገንብተን ለአገልግሎት በማብቃት ነው

97

ሚያዚያ 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) ‘’የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን ክፉ ህልም የምናመክነው በበቀል ተነሳስቶ ያወደማቸውን ተቋማት ቀድመው ከነበሩበት ሁኔታ በተሻለ ገንብተን ለአገልግሎት በማብቃት ነው’’ ሲሉ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር ገለፁ።

ዛሬ እየተካሄደ በሚገኘው የደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መውጫ ከተማን መልሶ ለመገንባት የተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፤ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ወቅት የፈረሱና የወደሙ ተቋማትንና መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

የክልሉን ህዝብ ውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ በማስቀጠል የአሸባሪውን ቡድንና ተላላኪዎቹን ህልም ለማምከን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የራስ ጋይንት ወረዳና የነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር ፈጥነው ወደ መልሶ ግንባታ መግባታቸው አረዓያነት እንዳለው ገልጸው፤ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የነፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙላው ጤናው በበኩላቸው ወረራው ካደረሰው ቁሳዊና የስነ ልቦና ጉዳት በፍጥነት ለመውጣት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመልሶ ግንባታ ሂደቱ መላው ህዝብና ሌሎች የልማት አጋሮች ከጎናችን መቆማቸውን በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ አረጋግጠናል ብለዋል።

በነፋስ መውጫ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ቴሌቶን ባለሃብቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችና ሌሎች አካላት የልማት አጋርነታቸውን በድጋፍ እያሳዩ ይገኛል።

አሸባሪው ህወሃት በንፋስ መውጫ ከተማ በወረራ በቆየባቸው ቀናት ከ236 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ዘረፋና ውድመት ማድረሱን በጥናት መረጋገጡም ተጠቁሟል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም 150 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም