ማህበሩ ለአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን የቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ለአረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን የቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ አደረገ

ደሴ ሚያዝያ 30/2014(ኢዜአ)በኢትዮጰያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ በደሴ ከተማ ለሚገኙ አረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን የቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ አደረገ።
ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቀን "ደግነት ለሰብዓዊነት" በሚል መሪ ሀሳብ በደሴ ከተማ መቄዶንያ ማዕከል እየተከበረ ነው።
የቅርንጫፉ ሃላፊ አቶ መላኩ ቸኮል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አቅመ ደካሞችንና አረጋዊያንን መንከባከብና መደገፍ የሁሉም ድርሻ ነው።
ማህበሩ አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተጎዱትንና ተፈናቃይ ወገኖችን በመደገፍ ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበር እንደነበር አስታውሰው፤የዘንድሮው በዓል ግን ለአረጋውያን ያለውን ክብር ለማሳየት ከአረጋዊያን ጋር ማክበሩን አመልክተዋል።
ለዚህም ከ380 ሺህ በላይ ብር ወጭ በማድረግ 200 ብርድ ልብስ፣ ከ500 በላይ ሳሙና፣ 200 ካርቶን የሐይጂን ኪትና ሌሎች የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
የደሴ መቄዶንያ ማዕከል ተወካይ ወይዘሮ አይናለም ታደሰ በበኩላቸው ማዕከሉ ከ300 በላይ አረጋዊያንና አዕምሮ ህሙማን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ከህብረተሰቡና ተቋማት ጋር በመተባበር ምግብና ቁሳቁስ እያቀረበ ቢሆንም፤ የአቅም ውስንነት ስላለበት ኅብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጠይቀዋል።
በከተማዋ የገቢ ማስገኛና የአዕምሮ ህሙማን ህክምና ማዕከል ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።
ድጋፉ ከተደረገላቸው መካከል አባ ተስፋ ጊዮርጊስ አለሙና አቶ ኢብራሂም አያሌው ማህበሩ ላደረገላቸው እገዛ አመስግነዋል።
ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን በዓለም ለ75ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ64ኛ ጊዜ ዛሬ እየተከበረ ነው።