ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት መስራት ይገባል

633

ሐረር ሚያዝያ 30/2014 (ኢዜአ) ... ባህላዊ እና ታሪካዊ ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ አስገነዘቡ።

ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ በሐረሪ ክልል በመከበር ላይ ባለው "የሸዋል ኢድ ”  በዓል የመክፈቻ ሥነሥርዓት ላይእንዳሉት “በርካታ ባህላዊ እሴቶችና አኩሪ ታሪክ ካላቸው ሀገሮች ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ” ነች።

ለአኩሪ ታሪኮቿም በሁሉም የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን አሻራ አስቀምጠዋል ሲሉ አመልክተዋል።

የሺ ዓመታት ታሪክ ባለቤት የሆነው የሐረሪ ክልልሕዝብም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ጭምር የስልጣኔ ምንጮችን ያበረከተና ታሪክና ቅርሶችን ለትውልድ እንዲተላለፉ የራሱን አሻራ የተወጣ ነው ብለዋል።

በተለይ ህዝቡ በፍቅር፣ በአብሮነት እሴቶች የበለጸጉ፣ በሰላም ወዳድነታቸው የታወቁ እና ህዝቦችን ተንከባክበው በጋራ የመኖር ባህልን ለሌሎች እሴቶችን ያካፈለ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሐረር የታሪክና የቅርስ ቱሩፋቶች ከሐረር አልፈው ለኢትዮዽያ ከዛም ባለፈ ለዓለም ዓቀፍ በመድረስ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ያስቻለ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም ሐረር  የክልሉ በሎም የሀገሪቱ የቱሪት መዳረሻ  በመሆኗ ባህላዊ እሴቶቿ፣ ሃይማኖታዊና ጥንታዊ ቅርሶቿ፣ ሙዚየሞቿ የጎብኚዎችን ቀልብ መሳባቸውንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ ቀጀላ ገለጻ እነዚህን ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና እና  ታሪካዊ ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ሁሉም አካል በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በክልሉ በአብሮነት፣በፍቅርና በአንድነት ለሚከበረው “የሸዋል ኢድ በዓል” መልካም በዓል እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት “ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

በዓሉ ሀገሪቱ ያላትን በርካታ ባህላዊ፣ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪዝም እምቅ ሀብቶች በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻነቷን ይበልጥ የሚያጎላ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በኢንቨስትመንት፣በዲፕሎማሲና በሌሎች መስኮች የሚደረገውን ርብርብ ለማጠናከር፣ ግንኙነትና ትስስርን ለመፍጠር እድል እንደሚከፍት ጠቁመዋል።

እንዲሁም “የሸዋል ኢድ” በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑንም አመልክተዋል።

የባህል፣የቅርስና ቱሪዝም ሀብቶችን በመጠበቅ፣በመንከባከብና በማበልጸግ ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አሟጦ ለመጠቀም የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር ነውም ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንን “አብሮነት፣ መከባበርና ፍቅር” ነው የሚገልጻቸው ያሉት ደግሞ “ከኢድ እስከ ኢድ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” ጣምራ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ናቸው።

ኡስታዝ አቡበከር እንዳሉት እንደነዚህ ዓይነት በዓላትና መድረኮች ይበልጥ መልካም እሴቶቻችንን ለሌላው አጉልተው  ያሳያሉ።

በዚህም ሁሉም ህዝብ አብሮነቱ፣ፍቅሩን፣መተሳሰቡንና መተጋገዙን ማዳበር ይገባል፤ ችግሮች ሲያጋጥሙም  በግልጽ በመነጋገርና በመመካከር መፍታት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም