የስራ ባህሉ የዳበረና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የአውራ አምባ ማህበረሰብ ሚና የጎላ ነው -ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

306

ባህር ዳር (ኢዜአ)፣ ሚያዚያ 30/2014 "በኢትዮጰያ የስራ ባህሉ የዳበረና አምራች ዜጋን ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት የአውራአምባ ማህበረሰብ ሚና የጎላ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋየ አስታወቁ።

የአውራ አምባ ማህበረሰብ 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።

ሚኒስትሯ በበዓሉ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ በርካታ ባህላዊ፣ ወጎች፣ ጥበቦችና ማህበራዊ መስተጋብሮች ያሉባት ድንቅ ሀገር ናት።

በመልካም የስራ ባህልና እሴቶች የታነፀ ማህበረሰብ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

አውራ አምባ በሃገራችን ተምሳሌት የሚሆኑ ድንቅ የስራ ባህል፣ የስርዓተ-ፆታ እኩልነት፣ ሁሉንም በኩል የሚያይና ባህላዊ ልዩነቶችን ለአንድነቱ ጥንካሬ መሰረት ያደረገ ማህበረሰብ ነው ብለዋል።

May be an image of 10 people, people standing and indoor

ማህበረሰቡ ለሰላም ዘብ የቆመ፣ ከፍ ያለ ክብር ያለውና ከህጻን እስከ አረጋዊ ተከባብሮና ተፋቅሮ የሚኖር ማህበረሰብ መሆኑን ሚኒስትሯ አመልክተዋል ።

"የአውራምባ ማህበረሰብ ትልቁ ሃብት የአስተሳስብ ሃብት መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው "ያሉት ዶክተር ኤርጎጌ በሀገራችን የስራ ባህሉ የዳበረና አምራች ዜጋ ለመፍጠር የአውራምባ ማህበረሰብ ሚናው ጉልህ መሆኑን አስታውቀዋል።

"የአውራ አምባ ማህበረሰብ ልማዳዊና ባህላዊ ክንዋኔዎችን ለአገር በሚጠቅም አግባብ በማሻሻልና አዳዲስ እሴቶችን በማስተዋወቅ ልምድ የሚቀመርበት ተቋም ሁኖ እያገለገለ ነው" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር ናቸው።

ማህበረሰቡ የስራ ፍቅሩ፣ታታሪነቱ፣ የጊዜ አጠቃቀም፣በወንዶችና በሴቶች መካከል ድንበር የሌለው የሰራ መስተጋብር የአውራምባ ማህበረሰብ እንቁ እሴቶች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ለመበታተን እየጣሩ ያሉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች እንደ አውራምባዎች ለፍላጎትና ለአላማ በአንድ በመቆም ቦታ ማሳጣት አንደሚገባ አሳስበዋል።

"የአውራምባ ማህበረሰብ በክልሉ ውስጥ ሁኖ ባሳየው ተምሳሌታዊ የስራ ባህል የበርካታ ግለሰቦችን ፣ቡድኖችን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ቀልብ በመሳብ የቱሪዝም መስህብ ሁኖ እየተጎበኘ ነው"  ብለዋል።

ሰላምን አንግቦ ልማትን ማፋጠን የአውራምባ ማህበረሰብ አላማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማህበረሰቡ መስራች ክቡር ዶክተር ዙምራ ኑሩ ናቸው።

ማህበረሰቡ ጠንካራ የስራ ባህልና ከአድሎ የፀዳ አሰራርን በመተግበር አሁን ላይ ሃሳቡ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልፀዋል።

የአውራ አምባ ማህበረሰብ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የሚገኝና በበርካታ የስራ ባህሎቹና ታታሪነቱ የሚታወቅ ነው።

በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ  የስራ ሀላፊዎችና የማህበረሰቡ አባላት በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም