የአገራዊ ምክክር አካታችነት እስከምን ድረስ?

224

የአገራዊ ምክክር አካታችነት እስከምን ድረስ?

  • አካታች አገራዊ ምክክር መሰረታዊ የሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም ህዝቡ ተቀራራቢና ለአገራዊ አንድነት ገንቢ የሆነ አቋም እንዲይዙ ለማድረግ አይነተኛ መንገድ ነው።
  • በአገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የተለያዩ ፓርቲዎችን በማካተትና  በትክክለኛ አካታችነት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳትና መተግበር አስፈላጊ ነው።

አገራዊ ምክክር በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የሃሳብ መሪዎችንና ቡድኖችን ወደ አንድ ጠረጴዛ በማምጣት በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በመምከርና ተመሳሳይ አቋም በመያዝ እንደ አገር መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት መሳሪያ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።

አገራዊ ምክክር በተለያዩ አገሮች የተለያዩ ስያሜዎች ሊኖሩት ቢችሉም የዝግጅት፣ ሂደትና ትግበራ የሚሉ ምዕራፎችን ማለፉ አንድ ያደርገዋል። የተለያዩ የአለም አገሮች በጦርነትና ሌሎች ችግሮችን ካለፉ በኋላ ወደ ግጭት የወሰዷቸውንና አላግባባ ያሏቸውን ጉዳዮች በሰለጠነ መንገድ በንግግር ለመፍታት አገራዊ ውይይት ማድረጋቸውን ሰነዶች ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያም በተለይም የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ልዩነት መፍታት ለአገራዊ አንድነት መሰረት በመሆኑ አካታች ውይይት ለማድረግ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ውይይቱን ለማስተባበር በዝግጅት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

በአንድ አገር አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ቀደም ሲል በውስጥ ከነበሩ ወይንም የሌሎች አገሮችን ልምድ በመውሰድ  ስህተቶችን ባለመድገም ውጤታማ ማድረግ ይገባል። የአካታችነትና አሳታፊነት ልክ፣ ውክልና እንዲሁም የአመራረጥ መስፈርቶች፣ አላማና ወሰን፣ የተቋማት አቀራረጽና የድጋፍ አወቃቀር እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ውሰጥ ሊቃኙ ከሚገቡት መካከል ይጠቀሳሉ።

ተሳትፎና አካታችነት

 አገራዊ ምክክር የተለያዩ ሃሳቦችና አመለካከቶች የሚንጸባረቁበት መድረክ ነው። አካታችችነት አገራዊ ምክክር ለማካሄድ በዝግጅት፣ ሂደትና ትግበራ ምዕራፎች ሁሉ አስፈላጊ መሆኑን የተደረጉ የጥናት ውጤቶች ያሳያሉ። በአገራዊ ምክክር ላይ የተጻፉ አብዛኞቹ ሰነዶች ትኩረት ሰጥተው እንደሚያመላክቱት ችግሮችን በውይይት በመፍታት መሰረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ማህበረሰቡን ያሳተፈ ከሆነ ብቻ ነው። በተወሰኑ የአፍሪካ አገሮች ላይ የተደረጉ አገራዊ ምክክሮችን መነሻ በማድረግ እንደ ጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር በ2009 “ከብሔራዊ ምክክሮች የሚወሰዱ ልምዶችና የስኬት ምንጮች” በሚል በእንግሊዝ በርንግሃም ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ልማት አማካሪ ሁማ ሃይደር ባደረጉት ጥናት ይህንኑ አመላክተዋል። በእኔነት ስሜት ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ከመነሻ ሃሳቡ ጀምሮ አካታችነት አስፈላጊ መሆኑንም በጥናታቸው ጠቁመዋል።  

የአካታችነት ደረጃ የተለያዩ የፖለቲካ ተዋናዮች፣ የሃሳብ መሪዎች፣ ማህበረሰብ አንቂዎች፣ ማህበረሰብ መሪዎች እንዲሁም የማህበረሰብ ክፍሎች መካተታቸው ቅሬታን በመፍታትና ተስፋቸውን እውን በማድረግ አገራዊ ምክክር አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን እንዲረዱ እድል ይሰጣል። ወጣቶች፣ ሴቶች፣ በተለያየ ምክንያት ከፖለቲካ ተሳትፎ የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በሂደቱ ማሳተፍና ሃሳባቸውን ማካተት እንዲሁም ጉዳያቸውን በአጀንዳነት መያዝ አስፈላጊ መሆኑን ሁማ ሃይደር በጹህፋቸው አስቀምጠዋል።

አገራዊ ምክክር ካደረጉ አገሮች አንዷ የሆነችው የመን ልምድ እንደሚያሳየው ሴቶችና ወጣቶችን በምክከሩ የኮታ አሰራርን በመጠቀም አሳትፋለች፣ በተቃራኒው ጆርዳን ባደረገችው ምክክር ሴቶችና ወጣቶችን የሚያሳትፍ ግልጽ አሰራር ተግባራዊ ባለማድረጓና በበቂ ሁኔታ በአጠቃላይ በምክክሩ ሂደት ያላቸውን ተሳትፎ እውቅና ሳትሰጥ መቅረቷን ሁማ ሃይደር በጹህፋቸው ዳሰዋል።

 በተጨማሪም የማህበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ ከፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያሌላቸውን ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ማሳተፍ ውጤታማነቱ ላይ አወንታዊ ተጽእኖ እንዳለው ያስቀምጣሉ። ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰፊ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ሂደት በተለያየ ምክንያት ከፖለቲካ ተሳትፎ የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ውክልናን በትክክል ለማካተት የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም እንደሚቻል የየመን አካሄድ በምሳሌነት ይነሳል። በአካታችነት ሂደት የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለማስቀረት በተለያየ ምክንያት ከፖለቲካ ተሳትፎ ለተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ስለ አገራዊ ምክክር ጠቀሜታ ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ይመከራል።ይህም በብቃትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ ለማድረግ እድል ይሰጣል። የምክክሩ ሂደት ከዝግጅቱ ጀምሮ አሳታፊነት የጎደለው ከሆነ በህጋዊነቱ፣ ባለቤትነትና ተቀባይነቱ ላይ ጥርጣሬን ያሳድራል።

 የተሳታፊዎች መጠን

የአገራዊ ምክክር ተሳታፊዎችን ብዛት የሚወስን ወጥ አሰራር የለም። እንደ ጉዳዩ ጥልቀትና ክብደት በአነስተኛ፣ መካከለኛና በርካታ ቁጥር ባለው ተሳታፊ ሊካሄድ ይችላሉ። የተሳታፊዎች ብዛት አገራዊ ምክክሩ የሚካሄድበት የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና የሚካሄድበት አውድና አላማዎች ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይችላል። የምክክሩ አላማ በአንድ ጉዳይ ላይ የሚወሰን ከሆነ ከጉዳዩ ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አካላት ሊያስፈልጉ ይችላሉ፤ በሌላ በኩል ምክክሩ አዲስ የማህበራዊ ግንባታ ለመመስረት ከሆነ ማህበረሰቡን የሚወክል በርካታ ቁጥር ያለው ተሳታፊን ያካተተ ተከታታይነት ያለው ውይይት ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ አገራዊ ምክክር ሰፊ እንቅስቃሴን የሚይዝ ሲሆን ከከፍተኛ ድርድሮች ጀምሮ በማህበረሰብ ዘንድ የሚፈጸሙ ሽምግልናዎችን ሊያካትት ይችላል። ተግባራዊ ሊደረገ የሚችልና ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሄ ማምጣትን አላማው አድርጎ የሚካሄድ ነው፤ ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን ዘላቂ መፍትሄ መስጠት፣ አገራዊ መግባባት መፍጠርና የጋራ አላማ ለወደፊት ማስቀመጥ ከአገራዊ ውይይት ዝርዝር አላማዎቸ ውስጥ ናቸው።

ውይይቶች በተለያየ መንገድ ሊካሄዱ ይችላሉ፣ በተለያየ አካላት ተነሳሽነትና አስተባባሪነት እንዲሁም የማህበረሰብ ክፍል ሊካሄዱ ይችላሉ። ከፍተኛ ደረጃ ወይንም በከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያካተተ (አብዛኛውን ጊዜ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ አሸማጋይነትና አነሳሽነት የሚካሄዱ)፣ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አነሳሽነት ለችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ ለማምጣት፣ ተአማኒነትን ለመጨመር የሚደረጉ፣ ለሰላምና መንግስት ግንባታ እንዲሁም የልማት እቅዶች የፖለቲካ ምክክር ከማድረግ የሚመጡ ይሆናል። ዜጎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡና የጋራ አቋም ለመያዝ እንዲያስችል፣ በተለያየ የማህበረሰብ ደረጃ የሚደረጉ ምክክሮችም አሉ።

የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በምክክሩ ለማካተት ጥረት ማድረግ ብቻውን ውጤታማ ምክክር ለማካሄድ ምቹ ሀኔታዎችን አይፈጥርም፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የሃይል አለመመጣጠን ካለ በተወሰኑ ቡድኖች ተጽእኖ ወይንም የበላይነት ውሰጥ ሊወድቅ ይችላል፣ ለአገራዊ ሽግግርና ከውይይቱ በኋላ ለሚጠበቁ ውጤቶች ሃይልን አመጣጥኖ መሄድ ተገቢ መሆኑን በኔዘር ላንድ ራድቦንድ ዩኒቨርስቲ የአንትሮፖሎጂ ጥናት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሳ ኢላያህ “አገራዊ ውይይት የእርስ በእርስ ጦርነትን ለማስቀረት”  በሚል  የየመንን ተሞክሮ ላይ ተመስርተው “ታይለር ኤንድ ፍራንሰስ ኦንላይን” በተሰኘ ማህበራዊ ገጽ ላይ በ2018 ባሳተሙት አርቲክል  አስገንዝበዋል።

በአገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ የተለያዩ ፓርቲዎችን በማካተትና  በትክክለኛ አካታችነት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ። የሴቶች፣ ወጣቶችና በተለያዩ ምክንያቶች ከፖለቲካ ተሳትፎ የተገለሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን የእምነት መሪዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን ማካተት ብቻ ሳይሆን በምክክሩ ሂደት በራሳቸው ጉዳይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ በውሳኔ ሰጪነት እንዲሳተፉና በሂደቱ ተጽእኖ እንዲያደርጉ እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አጽእኖት ሰጥተውታል።

የነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ድምጽ አለማካተት በምክክሩ ሂደት ጥርጣሬንና እርካታ አለማግኘትን ሊያስከትል ይችላል። በውሳኔ ሰጪነት የሚሳተፉ አካላትም ጉዳዩን በፈለጉበት መንገድ ሊያስኬዱት እንደሚችሉም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ላይ የአለም አቀፍ ልማት፣ ሰላምና ውይይት ስፔሻሊሰት ሄኒሪክ ሃርትማን “አገራዊ ምክክርና ልማት” በሚል ጹህፋቸው ላይ በስጋት አስቀምጠዋል።  

አካታች ምክክር ማድረግ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት መሰረት ቢሆንም ተሳታፊዎች በተለይም በምክክሩ መሳተፍ ያለባቸው ወሳኝ ሃይሎች ላለመሳተፍ ከወሰኑ የምክክሩ ሂደት ተቀባይነት ሊያጣ እንደሚችልም ስጋታቸውን ጨምረዋል። እዚህ ላይ በባህሬን በተካሄደው ምክክር “አል ወፋክ” የተሰኘው ተቃዋሚ ፓርቲ በምክክሩ የሚኖረው 5 መቀመጫ መሆኑን ሲያውቅ ራሱን ከምክክሩ ውጪ ማድረጉ የፈጠረውን አሉታዊ ተጽእኖ በማንሳት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ። በተመሳሳይ በጓቲማላ በ1989 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው ትልቅ አገራዊ ምክክር በተሳታፊዎች ላይ ባጋጠመ የደህንነት ስጋትና ወሳኝ የሚባሉ ሃይሎች እራሳቸውን ከውይይቱ በማግለላቸው ምክክሩ እንዲራዘም ተደርጓል።

በጆርዳንም በተመሳሳይ በተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል ተመጣጣኝ ውክልና በአገራዊ ምክክሩ እንዳልነበረና ሴቶችን፣ ወጣቶችንና ለዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍሎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በምክክሩ ማስተናገድ ባለመቻሉ ውክልናቸው ዝቅ እንዲል መደረጉን አስቀምጠዋል። በምክክሩ የተካተቱትም ቢሆኑ በገዥው መንግስት የተመረጡና የተመረጡበት መስፈርትም ግልጽነት የጎደለው በመሆኑ የህዝብ ተወካዮች መሆናቸው ላይ ጥርጣሬን ፈጥሮ ማለፉንና የምክክሩ ውጤት ተቀባይነት በማጣቱ የአገራዊ ውይይት የሚፈለገውን ግብ ማምጣት አለመቻሉንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የሆነ የሃሳብ ልዩነት፣ አለመግባባትና ተቃርኖ የሚታይ በመሆኑ፣ ሰፊ አገራዊ የህዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ አገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን “በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቅሚያ አዋጅ “ላይ ተደንግጓል።

በአካታችነት የአገራት ተሞክሮዎች

 የመን

የመን እንደ አገር ውይይት ማድረግ የጀመረችው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1960ዎቹ ጀምሮ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም “አገራዊ የምክክር ኮንፈረስ” በሚል ያካሄደችው የቅርብ ጊዜ ተደርጎ ይወሰዳል።

የመን በ2002 እና በ2010 የማያቋርጥ የፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብትና የጸጥታ ቀውስ ገጥሟት እንደነበር ይታወሳል፤  አላግባባያሉ አገራዊ ጉዳዮችን በውይይት በመፍታት ዴሞክራሲ የሰፈነባትና የየመን ፌደራል አስተዳደር ለመመስረት የሚያስችል አዲሰ እቅድ ለማውጣት አካታች አገር አቀፍ ውይይት ለማካሄድ እንዲያግዝ በ2013 የተባበሩት መንግስታትን፣ አውሮፓ ህብረት፣ ሩስያ፣ ቻይናና ሌሎችን ያካተተ አለም አቀፍ ቡድን በማቋቋም “እንርዳሽ” በሚል የእርስ በእርስ ጦርነቱን በእጅ አዙር ሲያስሄዱ የነበሩ አገሮች ውይይትም የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጣ ጣልቃ ገብነታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው ይነገራል።

ከአገራዊ የውይይት ኮንፈረንስ በፊት የሃውቲ አማጽያን ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ሳሌህ ጋር የየመንን ዋና ዋና ግዛቶች ለመቆጣጠር ጥምረት ፈጥረው ስለነበር የመንን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት በድጋሚ የከተተ ድርጊት ሆነ፤ በአጠቃላይ በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ከአገር አቀፍ ውይይት እኩል መካሄድ ጀመረ፤ ይህም ውይይቱ ለምን እንደሚካሄድ ጥያቄ ውስጥ የከተተና በአገሪቱ ጦርነትን እና አዲስ የሃውቲ አማጽያንን ከመቀስቀስ አልታደገም። ይህም በየመን ሰላም ለማምጣት የተካሄደው አገራዊ ውይይት የእርስ በእርስ ጦርነትን ያስከተለ በመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች የፖለቲካና ወታደራዊ ግጭቶችን ለማስቆም ትክክለኛ አካሄድ ወይንም መፍትሄ እንዳልነበር ይነገራል።

በሂደቱ አካታችነት ውጤታማ እንደነበር ፕሮፌሰር ሙሳ ኢላያህ በጹህፋቸው አስቀምጠዋል፣ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች ከፖለቲካ ውሳኔ ውጪ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካና ማህበራዊ ቡድኖች በጠረፔዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው እንዲመክሩ አስችሏል። በዚህም 30 በመቶ የሚሆነውን ለሴቶች እንዲሁም 20 በመቶ የሚሆነውን ለወጣት ተወካዮች የሰጠ ነበር። ልማት፣ የግለሰቦች መብት፣ በመንግስት የሃላፊነት ቦታ የሴቶች ተሳትፎና የጸጥታ ዘርፍ በስፋት በአገራዊ ምክክር ኮንፈረንሱ የተሰጡ ምክሮች ነበሩ፤ በአካታችነት በኩል ስኬቶች ይኑሩት እንጂ ምክክሩ ከመሰናክልና ችግሮች የጸዳ አልነበረም፤ ቴክኒካል ድጋፍ የሚሰጡ ሙያተኞች እጥረትና የፖለቲካ ድርድሮች ሲጀመሩ ችግር እንደገጠሙት ማንሳት ይቻላል።

የውይይት ተሳታፊዎች ለውይይት በሚቀርቡ አጀንዳዎችና የውይይቱ ሂደት ተአማኒነት ማጣት ለአጠቃላይ ሰላም ግንባታ የራሱ የሆነ ተጽእኖ መፍጠሩ ይነሳል። በመሆኑን በአገራዊ ምክክር ከጅማሬው ጀምሮ ተአማኒነት መፍጠር ውጤቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳለው በመግለጽ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሳ ኢላያህ “አገራዊ ውይይት የእርስ በእርስ ጦርነትን ለማስቀረት”  በሚል  የየመንን ተሞክሮ ላይ ተመስርተው የጻፉትን ጹህፍ ሃሳብ ይቋጫሉ ።

ሊቢያ

በሰሜን አፍሪካዊት አገር ሊቢያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 የአረብ ስፕሪንግን ተከትሎ የጀመረው የእርስ በእርስ ጦርነት መቋጫ ሳያገኝ ዛሬም ድረስ የአገሪቱ ሰላም መታመሙን ቀጥሏል። አላግባባ ላሉ ጉዳዮች መፍትሄ ለመፈለግ አገራዊ ምክክርን እንዲያስተባብር ከሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችና ማህበረስብ ተወካዮችን ያካተተ አገራዊ ምክክር ዝግጅት ኮሚሽን በ2013 ዓ.ም ተቋቋመ። በርካታ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎችን ማሳተፍ ውስንነቶች ተግባር ተደርጎ ይጠቀሳል። ሚሊሻዎችና የማዘጋጃ ቤት አመራሮችን በምክክሩ ለማካተት የተደረገው ጥረት አለመሳካቱ የአገራዊ ምክክሩን ተቀባይነት ዝቅ እንዲል አድርጎታል። በኢ-መደበኛ አካሄድ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ያላቸው የማህበረሰብ ተወካዮችን፣ በባህላዊ መንገድ ተሰሚነት ያላቸው መሪዎችን ዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍሎችና የሲቪል ማህበራትን ማሳተፍ አስፈላጊ አንደሆነ ይተነትናል። በተጨማሪም ለምክክሩ ተሳተፊዎች ግልጽ የሆነ አካታች ስትራቴጂና መመሪያ አለመኖር ለተአማኒነቱ መቀነስ ሌላው ጉዳይ ነው።

በሊቢያ የነበረው የጸጥታ ችግር እንዲሁም በፖለቲከኞች ዘንድ ለውይይት በቂ ዝግጅት አለማድረግ በምክክሩ ውጤታማነት ላይ ተጽእኖ ነበረው። አገራዊ ምክክር ዝግጅት ኮሚሽን ህዝብ በምክክሩ የሚያነሳቸውን ሃሳቦች ትርጉም ባለውና ውጤታማ በሆነ መንገድ አደራጅቶ መንግስት እንዲተገብር ለማድረግ የሚችልበት ቁመና ሳይኖረው ስራ መጀመሩም አገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ካላደረጉት ሁኔታዎች መካከል ይጠቀሳል።

በተመሳሳይ የአለም ባንክ ከአለም አቀፉ የዴሞክራሲና ምርጫ አስተባባሪ ተቋም ጋር በመተባበር በላቲን አሜሪካ አገሮች የተደረጉ አገራዊ ምክክሮችን ልምድ በሚዳስሰው ጹህፉ ጠቃሚ ልምዶችን አስፍሯል። ምክክሩ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ አገራዊ ፖሊሲ ለመቅረጽ በመደበኛ ተቋማት መፍትሄ ያላገኙ ችግሮችን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አላማ አድርጎ የተካሄደ ነው።

ምክክሩ ከቦሊቪያ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ኤልሳልቫዶር፣ ጉአቲማላ፣ ሜክሲኮና ሌሎች የላቲን አሜሪካ አገሮች የመንግስትና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች በተገኙበት በሁለት ምድብ በአንድ ቀን መርሃ ግብር የተካሄደ ነበር። ውይይቱ አሳታፊ፣ ግልጽና ለችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ከልብ የተካሄደ እንደነበር ጹህፉ ያስቀምጣል። በምክክሩ ጽኑ ድምዳሜ ላይ መድረስ ባይቻልም ግልጸኝነትን በማበረታታት በላቲን አሜሪካ አገሮች ያሏቸውን ሃብቶችና የብዝሃነት ልምድ በአገራዊ ምክክሩ እንዲካፈሉ እድል ፈጥሯል። ከተካሄዱት መካከል የሁለት አገሮችን እንደ ምሳሌ ማየት ይቻላል።

ቦሊቪያ

በቦሊቪያ የተደረገው አገራዊ ምክክር ከአካባቢ አስተዳዳሪዎች ጀምሮ የፖለቲካ ቡድኖችን፣ መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን በማካተት ከታች ወደ ላይ የተካሄደ ውይይት ነው። በማህበረሰብ ተቋማት ብዛትና በግዛት ወሰን ላይ ተመስርቶ የተሳታፊዎች ቁጥር ይጨምር ይቀንስ እንጂ በየደረጃው የተደረጉ ውይይቶች በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ የተካሄደ ነው፣ በጉዳዩ ላይ በመመስረት የሲቪል ማህበራት ድርጅት፣ የፓርላማ አባላት፣ የግዛት አስተዳደርና ሌሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል። የመንግስት ኢንቨስትመንትና ፋይናንስ፣ ለመንገድ መሰረተ ልማት በሚያዝ በጀት፣ አዲስ የታክስ መለያ መፍጠር፣ የንግድና ግብርና ፖሊሲ፣ የቤት ፖሊሲ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ የቢዝነስ ተቋማት አገራዊ ፖሊሲ፣ የከተማ ትራንስፖርት ፖሊሲና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መንግስት ከአምራች ዘርፉ ጋር ያደረገው ውይይትም ተጠቃሽ ነው።

መልካዓ ምድራቸውን ከግምት ውስጥ ያስገባ በእያንዳንዱ ክልሎች ስለሚኖሩ የልማት ስራዎች ልዩ ስምምነት፣ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ስለሚኖረው ግንኙነት፣ በመንግስትና አካባቢ አስተዳደሮች እንዲሁም የማዘጋጃ ቤት አስተዳዳሪዎች በአንድ ላይ በመቀራረብ የአስተዳደር ስራዎችን እንዲያከናውኑ ውይይቱ አመላክቷል። በእነዚህ ተግባራት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንዲሰራም እንዲሁ።

ኮሎምቢያ

በኮሎምቢያ አገራዊ ምክክር ማድረግ እንዲያስችል አስተባባሪ ተቋም በ1990 ተቋቁሞ ስራውን የጀመረ ሲሆን ለአገራዊ ውይይቱ መሰረት የሆኑ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለምክክሩ የሚያግዙ አስተያየቶችን፣ ምክረ ሃሳቦችን፣ ጥያቄዎችን፣ ጥቆማዎችን ለመሰብሰብ ህዝባዊ መድረኮችን አካሂዷል። ምንም እንኳ ከፍተኛ የተሳትፎ መጠን የታየበትና መጠነ ሰፊ የማህበረሰብ ክፍሎች ተወካዮችን ያሳተፈ ቢሆንም የተወሰነ ቡድን የበላይነት የታየበት እንደነበር ይገለጻል።  

አገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ

በኢትዮጵያ ሊካሄድ በዝግጅት ላይ የሚገኘው አገራዊ የምክክር መድረክ የእስካሁን ሂደት ተስፋ ሰጪ መሆኑ ይነገራል፣ አገራዊ መግባባት ሊኖርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አካታች የምክክርና የውይይት ሂደት ሰፊ መሰረታዊ የሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም ህዝቡ ተቀራራቢና ለአገራዊ አንድነት ገንቢ የሆነ አቋም እንዲይዙ ማድረግ የአካታች አገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ግብ መሆኑን በምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።

አገራዊ ውይይቶች ውጤታማ እና ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ግልጽ የሆነ መዋቅር ሊኖራቸው ይገባል። የሂደት ተአማኒነት በዋናነት ምክክሩን እንዲያሳልጥና እንዲመራ በሚሰየመው አካል ብቃት እና ገለልተኝነት ላይ የሚወሰን በመሆኑ ምክክሩን ለማስተባበር 11 ኮሚሽነሮችን ለመምረጥም በተለያዩ የመረጃ ዘዴዎች ከ600 በላይ እጩዎችን ህዝብ እንዲጠቁም ተደርጓል። ይህም ግልጽና አሳታፊ እንዲሁም አካታች በሆነ መንገድ መካሄዱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የእጩዎች ሹመት በጸደቀበት ወቅት ማስረዳታቸው ይታወሳል። የአፈ ጉባኤውን ሀሳብ የሚያጠናክሩት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ በእስካሁኑ ሂደት በተቻለ መጠን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድምጽ እንዲካተት መደረጉን በማስታወስ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማቋቋም ከወጡ አዋጆች በአንጻራዊነት የተሻለ ነጻነት፣ ገለልተኝነተና አሳታፊነት  የተረጋገጠበት አዋጅ መሆኑን ያስረዳሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው በእስካሁኑ ሂደት የተስተዋሉ መልካም ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች “በዝግጅት ምዕራፉ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የተፈለገውን ያህል አይደለም” ይላሉ። በቀጣይ ግን ኮሚሽኑ በሚያካሂዳቸው ተግባራት ላይ ፓርቲዎች የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መሥራት እንደሚገባ በአጽንኦት ያነሳሉ። የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ እንዲሆን የሁሉም ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሊሆን ይገባል፤ ለዚህም ኮሚሽኑ ከፓርቲዎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችለውን ሥራ ከምርጫ ቦርድ ጋር ጭምር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ደቻሳ አበበ ካለፈው የመበታተንና የግጭት ታሪክ በመማር መስማማትን፣ ለመነጋገር ዝግጁ መሆንን፣ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ማየትን፣ ሃሳቦችን ማክበርን በመላበስ አገራዊ ምክክሩን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ይመክራሉ። አለማዳላት፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ የአገር ጥቅምን በማስቀደም በሰከነ መንፈስት መነጋገር ተገቢ መሆኑን ጨምረዋል።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት አላግባባ ያሏቸው ልዩነቶች ላይ በጠረጴዛ ዙሪያ በመምከርና የጋራ አቋም በመያዝ በአገራዊ ምክክሩ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል። ችግሯን በውይይት በመፍታት የበለጸገች፣ ያደገች፣ ለዜጎች የምትመችና ለሌሎች አገሮች ታሪክ በምሳሌነት የሚጠቅሳት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ “ብልህ ከሌሎች ስህተት ይማራል” እንደሚባለው አገሮች ያካሄዱት የምክክር መድረክ ላይ በአካታችነትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከታዩ ችግሮች ልምድ መውሰድ ተገቢ ነው። ምክክሩ የኢትዮጵያውያን እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ያገባቸዋልና ሀሳባቸው ሊደመጥ ይገባል።