በግብርናው ዘርፍ የተጀመረውን ውጤታማ ስራ በአምራች ኢንዱስትሪው ለማስቀጠል ልንዘጋጅ ይገባል

162

ሚያዝያ 29/2014 (ኢዜአ) በግብርናው ዘርፍ የተጀመረውን ውጤታማ ስራ በአምራች ኢንዱስትሪው ለማስቀጠል ልንዘጋጅ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ።

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ አምራቾች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

'ኢትዮጵያ ታምርት' በሚል መሪ ሃሳብ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ይህንኑ በማስመልከት የዕውቅና መርሃ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የግል ዘርፍ አምራች ተዋናዮች በታደሙበት በ6 ዘርፎች ሽልማት ተካሂዷል።

በጥቃቅን፣ አነስተኛ፣ መካከለኛ፣ ከፍተኛ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አምራቾች እና የአምራች ማህበራት በሚል ስድስት ዘርፎች የተሰማሩ ውጤታማ የሆኑ አምራቾችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሸልመዋል።

የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅም፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ገቢ ምርቶችን የመተካትና ግብርን በታማኝነት መክፈል የቻሉ ተሸላሚዎች ሆነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በግብርና ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ጅምሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍም ለመድገም መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከመንግሥት አምስት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በመንግስት ጥረት ብቻ ለውጥ ስለማይመጣ የግሉ ዘርፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈታኝ ግን በአጭር ጊዜ የሚከፍል ወሳኝ የኢኮኖሚው ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻጋገር በትብብር መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

ዘርፉን የሚፈትኑ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው ፈተናዎችን በመቋቋም በውጭ እና በአገር ውስጥ ያለውን ሰፊ የገበያ ፍላጎት ተደራሽ ማድረግና ኢትዮጵያን ማበልጸግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ተሰፋ ሰጭ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ጠቅሰው መንግስት ለኢንዱስትሪዎች ድጋፍና ማበረታቻ መስጠቱን እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል።

የክልል መንግስታት እና አምራቾች ከተጋገዙ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ ከተወጡ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ዓላማ ኢንዱስትሪዎች ያጋጠማቸውን ችግር በመፍታትና ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ለማስቻል ነው ብለዋል።

የዘርፉን የስራ ባህል ማሳደግ፣ የምርቶችን ጥራት፣ አይነትና ተወዳዳሪነት የማሻሻልና የውጭ ምንዛሬ ግኝቶችን ማሳደግ እንዲሁም የገቢ ምርቶችን የመተካት አቅምን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነም ገልጸዋል።

በኮቪድ 19 እና በአ ሸባሪው የሕወሃት ቡድን ወረራ ጉዳት ያጋጠማቸው ኢንዱስትሪዎች በችግር ውስጥ ሆነው እንኳን ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እና ግብር በመከፍል ሃላፊነታአቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል።

የዘንድሮው ኤክስፖርት አፈጻጸማቸው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ37 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

ኢ-ተገማች በሆነው ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ እንደ አገር ለመቀጠል የዜጎችን ፍላጎት የሚያሟላ በቂ ምርት ማምረት እንደሚገባ፣ ለዚህ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ቀጣይነት ባለው አግባብ መፈጸምን አለብን ነው ያሉት።

አምራች ኢንዱስትሪው በ2012 ከነበረበት በ2022 ዓ.ም በኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ከ6 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ከ50 በመቶ ወደ 85 በመቶ፣ ከውጭ ገቢ ምርቶች የመተካት አቅማቸውን ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘውን 400 ሚሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ግቦች መቀመጣቸውንም አውስተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሸላሚዎች፤ ሽልማቱ  በምርታማነት፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝትና ስራ እድል ፈጠራ ረገድ ይበልጥ እንድንሰራ የሚያበረታታን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም