በልዩ ወረዳው ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ያደረሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ለህግ አሳልፈን እንሰጣለን- የአከባቢው ነዋሪዎች

132

አርባ ምንጭ ፤ ሚያዚያ 29 ቀን 2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል ደራሼ ልዩ ወረዳ በቅርቡ የፀጥታ ችግር ፈጥረው ሰብዓዊ ጉዳት ያደረሱ ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ለህግ አሳልፈው በመስጠት የአካባቢያቸውን ሰላም ለመመለስ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ የአከባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡

በዴራሼ ልዩ ወራዳ በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር በመፍታት ወደቀደመ ሰላሙ ለመመለስ የተደራጀው የፀጥታ ጥምር ኃይል ከተለያዩ የኅህበረሰብ ክፍሎች ጋር በጊዶሌ ከተማ ተወያይቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የዴራሼ ልዩ ወራዳ ማህበረሰብን በማይወክሉ ጥቂት ጽንፈኛ የጥፋት ቡድኖች በተፈጠረው የፀጥታ ችግርና በደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት  ማዘናቸውን ገልጸዋል፤ ድርጊቱንም አውግዘዋል።

ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብረው በህገ-ወጥ መንገድ የታጠቁ ፀረ-ሰላም አካላትን ለህግ አሳልፈው በመስጠት የአካባቢያቸውን ሰላም ለመመለስ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የአከባቢውሀገር ሽማግሌዎች አቶ እሸቱ ማምዴና አቶ ገልገሎ ጉይታ በሰጡት አስተያየት ችግሩ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል።

“የአካባቢው ማህበረሰብ ባህልና ወግ በማይፈቅድ መልኩ በህገ-ወጥ  መንገድ ታጥቀው ችግር የፈጠሩ አካላትን ለህግ  አሳልፈን እንሰጣለን” ሲሉ አስታውቀዋል።

ሌላኛው ተሳታፊ አቶ ባደገ ፈጠነ በበኩላቸው ወጣቱን ለጥፋት በማደራጀት የሚንቀሳቀሱና ህገ-ወጥ መሣሪያ የታጠቁ አካላት አጋልጠው ለህግ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

አቶ ባደገ አክለውም “የደራሼ ልዩ ወረዳ ህዝብን ለማዳን ፀረ-ሰላም ኃይሎችን ለህግ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

የፀጥታ ጥምር ኃይል ሰብሳቢ ሌተናል ኮሎኔል ፈጠነ ሲሳይ እንዳሉት በአካባቢው የተፈጸመው ድርጊት እጅግ ፀያፍና ሊወገዝ የሚገባ ነው።

“የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ በልማት ላይ ማትኮር በሚገባን ወቅት ችግሩ መፈጠር አልነበረበትም ” ብለዋል።

ሌተናል ኮሎኔል ፈጠነ  አክለው ህዝቡ ከፀጥታ ጥምር ኃይል ጋር በመቀናጀት በሚቀጥሉት ቀናት ህገ-ወጥ ታጣቂዎቹን ለህግ ለማቅረብ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

 ከግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ተከፍተው የህዝብ አገልግሎት መስጠት መጀመር አለባቸው ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ መንግሥት ጋር በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ አካባቢውን የማረጋጋት፣ ሰላሙን የመመለስና የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን በመለየት ከሕዝብ ጋር ሆኖ ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑም ቀደም ሲል ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።