በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመከላከል የቅድመ ጽንሰት ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ ተመለከተ

173

ሀዋሳ፣ ሚያዝያ 29/2014 (ኢዜአ) በእርግዝና ወቅት የሚከሰቱ ውስብስብ የጤና ችግሮችን ለመከላከል የቅድመ ጽንሰት ምርመራ ማድረግ እንደሚገባ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በቅድመ ጽንሰት ዙሪያ ባካሄደው የምርምር ውጤት መሰረት የቅድመ ጽንሰት ጤና አገልግሎት በደቡብና ሲዳማ ክልሎች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ሊጀመር ነው።

ኮሌጁ በምርምር ውጤቱ አተገባበር ዙሪያ ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም  ከደቡብና ሲዳማ ክልል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ላይ በዩኒቨርሲቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መሪ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፈሰር ዶክተር አንዳርጋቸው ጣሰው እንዳሉት በእርግዝና ወቅት በእናቶችና ጽንሱ ላይ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን ለመከላከል የቅድመ ጽንሰት ምርመራ ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው።

እናቶች መውለድ በሚያስቡበት ወቅት ከመጸነሳቸው ሶስት ወራት አስቀድመው ምርመራ በማድረግ አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

"የደም ማነስ ችግር፣ የሰውነት የክብደት መጠን፣ እንደ ስኳርና ሌሎች ተያያዥ በሽታዎች ያሉባቸውና መድሀኒት የሚወስዱ እናቶች የቅድመ ጽንሰት ምርመራ ካላደረጉ በእርግዝና ወቅት ውርጃ፣ በማህጸን ጽንሱ የመሞት፣ ለአካል ጉድለትና ሌሎች በሽታዎች ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።

ችግሩን ለመከላከል በተደረገ ምርምር ላይ በመመስረት የቅድመ ጽንሰት የጤና አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ በሲዳማና ደቡብ ክልል በተመረጡ አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል።

በጤና ሚንስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት የጤና ቡድን አስተባባሪ ሲስተር ዘምዘም መሀመድ በበኩላቸው እንዳሉት በሀገሪቱ ከእናቶችና ህጻናት ጤና ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።

በተለይ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችንና የጽንስ መቋረጥን እንዲሁም የህጻናትን ሞት ለመቀነስ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ጥንዶች መውለድ ሲያቅታቸው ምክንያቱን ለማወቅ ከሚያደርጉት የጤና ምርመራ ባለፈ የቅድመ ጽንሰት ምርመራ እንዳልተለመደ ተናግረዋል።

"መውለድ የሚፈልጉ ሴቶች ከእርግዝና በፊት የቅድመ ጽንሰት ምርመራ ማድረጋቸው ያሉባቸውን የጤና፣ የምግብ እጥረት፣ የደም ማነስና ሌሎች ችግሮችን በመለየት አስቀድመው እንዲታከሙ በማድረግ ጤናማ ህጻን ለመውለድ ያስችላቸዋል" ብለዋል።

እናቶች የሚሰሩባቸው አካባቢዎች በእርግዝና ወቅት ጉዳት ሊያስከትሉ የሚያስችሉ ለጨረርና ኬሚካል የሚያጋልጡ ከሆነ ውርጃ እንዳያጋጥማቸው፣ ለሌላ በሽታ እንዳይጋለጡና አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳይወልዱ የቅድመ ጽንሰት ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቀዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ታፈሰ ማቲዮስ በስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡን የጠቀሙ በርካታ ምርምሮችን በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤናና በሌሎች መስኮች አከናውኗል።

በአሁኑ ወቅትም ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ከ28 በላይ ምርምሮችን በጤናው ዘርፍ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በእናቶችና በጽንስ ላይ የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመፍታት የተካሄደው ምርምር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ እንዲሆን መፈቀዱን ዶክተር ታፈሰ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም