ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ አምራቾችን ሸለሙ

118

ሚያዝያ 29/2014 ( ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ አምራቾችን ሸለሙ።

‘ኢትዮጵያ ታምርት’ በሚል መሪ ሃሳብ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለመ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ይህንኑ በማስመልከት የዕውቅና መርሃ ግብር የተዘጋጀ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም የግል ዘርፍ አምራች ተዋናዮች በታደሙበት በ6 ዘርፎች ሽልማት ተካሂዷል።

በጥቃቅን፣ አነስተኛ፣ መካከለኛ፣ ከፍተኛ፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አምራቾች እና የአምራች ማህበራት በሚል ስድስት ዘርፎች የተሰማሩ ውጤታማ የሆኑ አምራቾችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሸልመዋል።

የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት አቅም፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ገቢ ምርቶችን የመተካትና ግብርን በታማኝነት መክፈል የቻሉ ተሸላሚዎች ሆነዋል።

“የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ዓላማ ኢንዱስትሪዎች ያጋጠማቸውን ችግር በመፍታትና ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል ነው።

የዘርፉን የስራ ባህል ማሳደግ፣ የምርቶችን ጥራት፣አይነትና ተወዳዳሪነት የማሻሻልና የውጭ ምንዛሬ ግኝቶችን ማሳደግ እንዲሁም የገቢ ምርቶችን የመተካት አቅምን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።

አምራች ኢንዱስትሪው በ2012 ከነበረው በ2022 ዓ.ም ወደ የኢኮኖሚ ድርሻውን ከ6.8 በመቶ ወደ 17.2 በመቶ፣  50 በመቶ የማምረት አቅማቸውን ወደ 85 በመቶ፣ የገቢ ምርቶች የመተካት አቅማቸውን ከ30 በመቶ ወደ 60 በመቶ እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘውን 400 ሚሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊዮን ማሳደግ ግብ ተወስቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በግብርና የተጀመረውን ውጤታማ ስራ በኢንዱስትሪው ዘርፍም የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከመንግሥት አምስት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በመንግስት ጥረት ብቻ ለውጥ ስለማይመጣ የግሉ ዘርፍ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የክልል መንግስታት እና አምራቾች ከተጋገዙ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ ከተወጡ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ሲሉ ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ገቢ ምርቶችን መተካት ላይ  በማተኮር ከፍተኛ ገበያ ፍላጎትን ማሟላት ይገባል፤መንግስት ከጎናችሁ ነው ሲሉም አበረታተዋል።